ቀጥታ፡

ቢሮው ተግባራዊ ያደረጋቸው በቴክኖሎጂ የተደገፉ አዳዲስ አሠራሮች የከተማዋን የገቢ አቅም አሳድጓል 

አዲስ አበባ፤ሰኔ 22/2018(ኢዜአ)፦ተግባራዊ ያደረጋቸው በቴክኖሎጂ የተደገፉ አዳዲስ አሠራሮች የአገልግሎት አሰጣጡን ከማዘመን ባለፈ የከተማዋን የገቢ አቅም ማሳደጉን የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ፡፡    

ቢሮው ቀደም ሲል ግብር ከፋዮች በአካል በመቅረብና የወረቀት ሰነዶችን በመያዝ ያገኙት የነበረውን አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ ወደ ኦንላይን ሥርዓት ማሸጋገር ችሏል።

የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ የሞደርናይዜሽን ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ መሃመድ አብዱረህማን ለኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ ቢሮው ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ የሪፎርም ሥራዎችን አከናውኗል። 

ግብር ከፋዮች በአካል ሳይመጡ በኢሜል እና በተዘረጋው የኦንላይን ሊንክ አገልግሎቱን ማግኘት እንዲችሉ ከፌደራል ገቢዎች ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት የተቀናጀ የልማት ሥርዓት ተዘርግቶ ወደ ተግባር መገባቱን ጠቁመዋል።

ይህ አዲስ አሠራር ግብር ከፋዮች ባሉበት ሆነው አገልግሎት የሚያገኙበትን ምኅዳር የፈጠረ ሲሆን፣ የባለቤትነት ስም ዝውውርን ጨምሮ የተለያዩ የሕግ ተገዥነት አገልግሎቶችን ያካተተ መሆኑን አስረድተዋል።

ቢሮው በራሱ አቅም ያለማውን የዕዳ ክትትል ሥርዓት ወደ ተግባር በማስገባቱ በ17ቱም ቅርንጫፎች የሚወሰኑ የዕዳ ውሳኔዎችን በቅርበት ለመከታተልና የሚሰበሰበውን ገቢ ወደ ገንዘብ በመለወጥ ረገድ ከፍተኛ አፈጻጸም ተመዝግቧል።

የክሊራንስ አሰጣጥ ሂደቱን ይበልጥ ግልጽ፣ ቀልጣፋና እምነት የሚጣልበት ለማድረግ ባርኮድ ያለው አዲስ የኦንላይን አሠራር ተግባራዊ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ 

የተዘረጉት የዲጂታል አገልግሎቶች ግብር ከፋዮች ባሉበት ሆነው ግብራቸውን እንዲያሳውቁና እንዲከፍሉ በማድረጉ፣ በየወሩ መጨረሻ ላይ በቅርንጫፍ ቢሮዎች ይታይ የነበረውን ከፍተኛ መጨናነቅና የረጅም ጊዜ ጥበቃ ማስቀረት መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡ 

ቢሮው በቀጣዩ በጀት ዓመትም የደረጃ "ለ" ግብር ከፋዮችን የሚያስተናግደውን የኢቲ ታክስ (eTax) ሥርዓት ሙሉ ለሙሉ ወደ ዲጂታል በማሸጋገር፣ ግብር ከፋዮች ባሉበት ሆነው አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችሉ ማሻሻያዎችን እንደሚተገብር ገልጸዋል።

በከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ የኤሌክትሮኒክስ ታክስ ግብይት ድጋፍና ክትትል የሥራ ሂደት ተወካይ አቶ ሰይድ መሃመድ፤ ለግብር ከፋዮች ስለ አገልግሎቱ አጠቃቀም በቂ ስልጠናና ተከታታይ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። 


 

የቅርንጫፉ የኤሌክትሮኒክስ ታክስ ክፍያ አሰባሰብና ክትትል ቡድን አስተባባሪ ተወካይ አቶ ኢድሪስ መሃመድ በበኩላቸው፣ አዲሱ የዲጂታል ሥርዓት ተቋማዊ አፈጻጸምን ከማሳደግና ሥራዎችን ከማቅለል አንጻር ሰፊ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል።


 

የቅርንጫፉ ተገልጋዮችም በአዲሱ አሠራር መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

አዲሱ የኦንላይን ሥርዓት ረጅም ሰልፍን ያስቀረና ተገልጋዩ በቤቱ ሆኖ ሁሉንም አገልግሎት ማግኘት እንዲችል ያደረገ መሆኑን እና በዚህም ዘርፈ-ብዙ ጥቅሞችን እንዳስገኘላቸው ተናግረዋል፡፡ 


 

የዲጂታል አሠራሩ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ በማስቻል ይደርስባቸው የነበረውን ከፍተኛ እንግልት ሙሉ በሙሉ ማስቀረቱንም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም