ኢትዮጵያ በእናቶችና ህጻናት ሞት ቅነሳ ለአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት የሚሆኑ ውጤታማ ተግባራትን አከናውናለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በእናቶችና ህጻናት ሞት ቅነሳ ለአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት የሚሆኑ ውጤታማ ተግባራትን አከናውናለች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በእናቶችና ህጻናት ሞት ቅነሳ ለአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት የሚሆኑ ውጤታማ ተግባራት ማከናወኗን የጤና ሚኒስትር መቅደስ ዳባ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
በአፍሪካ የሕፃናት፣ የሴቶችና የጎልማሶች ጤና እና ሥርዓተ ምግብን ማሻሻልን ዓላማ ያደረገው የካውንትዳውን 2030 ዓመታዊ አህጉራዊ ጉባኤ ከ36 የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ የጤና ዘርፍ ፖሊሲ አውጪዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
ጉባኤው ሀገራዊ የሆኑ መረጃዎችንና ሳይንሳዊ የመረጃ ምንጮችን በስፋት መሰብሰብና መተንተን ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ የተተነተኑትን መረጃዎች ለጤና ፖሊሲ ፍትሐዊ ተደራሽነት እና ለሥርዓተ-ጤና ግንባታ ጠቃሚ ግብዓት እንዲሆኑ ማስቻልን ዓላማ ያደረገ ነው።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በጉባኤው መክፈቻ፤ ጉባኤው የ2030 የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት፣ በተለይም በእናቶችና በጨቅላ ሕፃናት ጤና ላይ የተሰሩ ሥራዎች ምን ያህል ለውጥ አመጡ የሚለውን ሀገራት በጋራ የሚገመግሙበት መድረክ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያም በእናቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሰውን ሞት በከፍተኛ ደረጃ መቀነሷን በተመለከተ ልምድና ትምህርት የምታጋራበት መድረክ እንደሚሆንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በተገበረቻቸው ዕቅዶች በእናቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሰውን ሞት በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ መቻሏንና ይህ ተሞክሮ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ምሳሌ መሆኑን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ በሽታዎችን በመቆጣጠር በኩል በርካታ ውጤቶች ማስመዝገቧን የጠቀሱት ዶክተር መቅደስ፤ በተለይም በቅርብ ጊዜ የማርበርግ ወረርሽኝን በፍጥነት መቆጣጠር መቻሏን በማሳያነት አስታውሰዋል።
ይህንን ተሞክሮ ሌሎች ሀገራት ልምድ እንዲወስዱበት እንደሚደረግም አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ በእናቶችና ሕፃናት ሞት ቅነሳ፣ በዘላቂ የጤና ግቦች፣ በተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች እንዲሁም በወረርሽኝ መከላከል ላይ በቂ አቅም እየገነባች መሆኑን ጠቁመው፤ ሀገራትም በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው፤ መርሃ ግብሩ በዘላቂ የልማት ግቦች ላይ የተቀመጡ ዋና ዋና አመላካቾችን አፈጻጸም በሳይንሳዊ የመረጃ ምንጮች በመሰብሰብና በመተንተን ለጤናው ዘርፍ ግብዓት እንዲሆን ለማድረግ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
በተለይም እንደ ሀገር የተነደፉ የጤና ግቦችን ከዓለም አቀፍ የዘላቂ ልማት ግቦች ጋር በማናበብ፣ በሂደቱ የሚስተዋሉ ችግሮችንና ክፍተቶችን ቀድሞ መለየት እንደሚያስችል አስገንዝበዋል።