ቀጥታ፡

ዘላቂና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይልን በሁሉም አካባቢ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂ እየተዘጋጀ ነው

አዲስ አበባ፤ሰኔ 22/2018(ኢዜአ)፦ዘላቂና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይልን በሁሉም አካባቢ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂ እየተዘጋጀ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የብሔራዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት መርሃ ግብር ምዕራፍ ሦስት ትግበራን የተመለከተ አውደጥናት አካሂዷል።


 

በዚህ ወቅት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የኤሌክትሪክ ኃይል ለዕድገትና ለማንኛውም ዓይነት የልማት እንቅስቃሴ ወሳኝ ነው።

በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብ ታዳሽ፣ ዘላቂና አስተማማኝ የኃይል ተደራሽነት የኢትዮጵያን ብልፅግና፣ ዕድገትና ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።


 

ኢትዮጵያ ያሏትን የኃይል አማራጭ ምንጮች ለመጠቀም የኃይል ማመንጨት አቅምን ማሳደግ፣ እንዲሁም የኃይል አማራጮችን የማሻሻል ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ለብሔራዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት መርሃ ግብር ትግበራ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲያድግ ለማድረግ የኢነርጂ ፖሊሲ ክለሳ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም መንግሥት ዘርፉን ለማጠናከር በርካታ ስትራቴጂዎችንና የሕግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

የመጀመሪያውና ሁለተኛው የኤሌክትሪክ ተደራሽነት መርሃ ግብር ትግበራ ከዋናው መስመር ርቀው ባሉ አካባቢዎች የሶላር ቴክኖሎጂዎችን ለገጠሩ ማኅበረሰብ ተደራሽ በማድረግ ረገድ መሻሻል ያመጣ መሆኑን አብራርተዋል።

በመርሃ ግብሩ የሦስተኛው ምዕራፍ ትግበራም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ንጹሕ ኢነርጂን ማስፋፋት፣ ለምርታማነት ተግባራት ቅድሚያ መስጠትና የዘርፉን ዲጂታላይዜሽን አሠራር ማጠናከር ላይ የሚያተኩር መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህ ምዕራፍ ትግበራ ከ18 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው በሁለቱ ምዕራፎች ያጋጠሙ ክፍተቶችን ለመፍታት በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

ቀጣናዊ የኃይል ትስስርን በማጠናከር ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ኃይል በማቅረብ የአህጉሪቱን ሁለንተናዊና የተቀናጀ ልማት በማሳለጥ ቀጣናዊና አህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደትን ለማጠናከር እየተሠራ መሆኑንም አስረድተዋል።


 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ፤ የኃይል ማመንጫ፣ ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ ሥራዎች ይጠናከራሉ ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ትግበራ እስከ 2035 ድረስ ባሉት ዓመታት የኤሌክትሪክ ኃይልን በመላ አገሪቱ ለማዳረስ መታቀዱን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው ናቸው።


 

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኤሌክትሪፊኬሽንና ኢነርጂ መረጃ መሪ ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ዳቢ፤ የብሔራዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን የሚመራ ስትራቴጂ ለማዘጋጀት ከአንድ ዓመት በላይ ጥናት ሲካሄድ ቆይቷል ብለዋል።


 

በስትራቴጂው የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት መንግሥት፣ ከልማት አጋሮችና ከግሉ ዘርፍ ጋር በትብብር እንደሚሠራም ገልጸዋል።

የዓለም ባንክ የኢነርጂ ባለሙያ ወንድአየሁ ደምሴ በበኩላቸው፤ ባንኩ በኢነርጂ ዘርፍ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በትብብር እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

አሁንም በብሔራዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት መርሃ ግብር የቴክኒክ ድጋፍ ማድረጉንና በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም