ቀጥታ፡

የገጠር ሞዴል መንደር አኗኗራችንን ከማዘመነኑ ባለፈ ለተሻለ ሥራ አነሳስቶናል 

ቦንጋ፤ ሰኔ 22/2018(ኢዜአ)፦ የገጠር ሞዴል መንደር አኗኗራችንን ከማዘመኑ ባለፈ ለተሻለ ሥራ እንዳነሳሳቸው በካፋ ዞን የጊምቦ ወረዳ ሞዴል የገጠር መንደር ተጠቃሚዎች ገለጹ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ሰሞኑን በካፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ የተገነባውን የገጠር ሞዴል መኖሪያ መንደር መመረቃቸው ይታወሳል፡፡

የገጠር ሞዴል መኖሪያ መንደር የገጠሩን ማህበረሰብ የኑሮ ደረጃ ለማሻሻልና ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገውን ፍልሰት ለመቀነስ አልሞ የተቀየሰ ነው።

በካፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ በተገነቡ የገጠር ሞዴል መኖሪያ ቤቶች ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል አርሶ አደር ጌታቸው ሽፈራው የመጠጥ ውሃ፣ የኤሌክትሪክ ሀይልና ሌሎች አገልግሎቶች የተሟላለት የገጠር ሞዴል መኖሪያ መንደር የህብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ ቀይሮታል።

የግብርና ባለሙያዎችን ምክረ ሀሳብ መነሻ በማድረግ የተገነቡ መኖሪያ ቤቶች ንጹህና ለኑሮ ምቹ ከመሆናቸው ባለፈ የከብቶች በረትም ከሰዎች መኖሪያ ቤት ተለይተው መገንባታቸውን ጠቁመዋል።

በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው በሞዴል መንደሩ የአመጋገብ ሥርአታቸውን ለማስተካከል በጓሯቸው አትክልቶችን እያለሙ እንደሆኑና በዚህም ለሌሎች አርአያ ለመሆን እንደሚተጉ ተናግረዋል።

ሞዴል መንደሩ የአርሶ አደሩን አኗኗር ከመሠረቱ እንዲቀየር መንግስት በቁርጠኝነት የሰራበት መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው የዚሁ ወረዳ አርሶ አደር ተሾመ ገብሬ ናቸው።

ሞደል የገጠር መንደሩ በመኖሪያ ቤታቸው ዙሪያ የሌማት ትርፋት ፓኬጆችን ለማከናውን ምቹ ሁኔታን በመፍጠሩ ተጨማሪ የገቢ አቅም እንደሆናቸውም ተናግረዋል።

ቀደም ሲል የእንስሳትና የሰው መኖሪያ የተቀላቀለ በመሆኑ ለኑሮ ምቹ እንዳልነበር ገልጸው ሞዴል መንደሩ ኑሯቸውን እንዳዘመነውና የኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።

አርሶ አደር ታዬ ታከለ በበኩላቸው የግብርና እና አካባቢ ጥበቃ ሥራቸውን ከጓሮ አትክልት ልማት ጋር በማያያዝ የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ በትጋት እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ዘመናዊ አኗኗራቸው የቆሻሻ አወጋገድ ስርአታቸውን በማዘመን ንጽህ አካባቢን ከመፍጠር ባለፈ ቆሻሻን ለተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዋል ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው አስረድተዋል።

የገጠር መኖሪያ መንደሩ በአንድ አካባቢ በማሰባሰብ ማህበራዊ ግንኙነታቸውን ከማሳደግ ባለፈ በተለያዩ መሰረተ ልማቶች ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እንዳገዛቸው ተናግረዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የግብርናና ገጠር ሽግግርን እውን በማድረግ የአርሶ አደሩን አኗኗር ለማዘመን እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የገጠር ሞዴል መንደር የመብራት፣ የውሃ፣ የመንገድን ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶችን አርሶ አደሩ በአቅራቢያው ማግኘት የሚያስችልና የኢኮኖሚ አቅሙን የሚያሳድጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም ተግባሩን በማስፋት ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግን ፍልሰት ለማስቀረት በቁርጠኝነት እንሰራለን ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም