ቀጥታ፡

የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት የኢትዮጵያን የልማት ትልሞች በሚያረጋግጥ መልኩ የተዘጋጀ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2018(ኢዜአ)፦ የ2019 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀት የኢትዮጵያን የልማት ትልሞች በሚያረጋግጥ መንገድ መዘጋጀቱን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ።

ቋሚ ኮሚቴው የመንግሥት ተቋማት የተመደበላቸውን በጀት በጥንቃቄና በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል እንዳለባቸውም አሳስቧል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ 2019 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀት ላይ ከገንዘብ ሚኒስቴርና ከባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ጋር የማጠቃለያ ውይይት አካሂዷል።


 

በመድረኩ የረቂቅ በጀቱን ዝርዝር ማብራሪያ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፤ 2019 በጀት ዓመት በጀት የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን መነሻ አድርጎ መዘጋጀቱንና በአጠቃላይ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን ይበልጥ የሚደግፍ መሆኑን ገልጸዋል።


 

2019 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀት ጠቅላላ መጠን 2 ትሪሊየን 339 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ሲሆን፥ ይህም 2018 በጀት ዓመት በጀት ጋር ሲነጻጸር 21 ነጥብ 3 በመቶ ጭማሪ አለው።

የበጀት ድልድሉ ለመደበኛ በጀት 1 ትሪሊየን 236 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ይህም እየተገባደደ ከሚገኘው በጀት ዓመት አንጻር 16 ነጥብ 5 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ብለዋል፡፡

በሌላ መልኩ ለካፒታል በጀት 568 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር እንዲሁም ለክልሎች የሚደረግ ድጋፍ 520 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች በየዓመቱ እያደገ የመጣው በጀት የሕዝቡን መሠረታዊ ጥያቄዎችና ፍላጎቶች እየፈታ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ 

ይሁን እንጂ በጀታቸውን በአግባቡ ባልተጠቀሙና ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ አካላት ላይ ምን ዓይነት እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሚገኙ ጠይቀዋል። 

በተጨማሪም የመንግሥት ተቋማት የነዳጅ አጠቃቀም ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ፥ ተቋማትን ከነዳጅ ጥገኝነት በማላቀቅ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች (EV) ለማሸጋገር ምን ዓይነት ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ጥያቄ አቅርበዋል።

ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፤ በአሠራር ረገድ ክፍተት በተገኘባቸው አካላት ላይ ተጠያቂነትን የማስፈን ሥራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት ከአስተዳደራዊ ቅጣት ጀምሮ አስተማሪ የሆኑ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

አጠቃላይ በጀቱ ሀገራዊ ዕድገትንና የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን በሚያረጋግጥ መልኩ የተዘጋጀ በመሆኑ ተቋማት የተመደበላቸውን የሕዝብ ሀብት በጥንቃቄ ማስተዳደር እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጆ በበኩላቸው፤ 2019 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀት በጥሩ ሁኔታ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በጀቱ የኢትዮጵያን የልማት ትልሞች የሚያሳካ መሆኑን ጠቁመው ተቋማት የተመደበላቸውን በጀት በጥንቃቄ ሥራ ላይ ማዋል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ቋሚ ኮሚቴው በረቂቅ በጀቱ ላይ ያደረገውን ግምገማ በማጠናቀቅ በቀጣዩ ሳምንት ለምክር ቤቱ የውሳኔ ሐሳብ እንደሚያቀርብ ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም