የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ዲጂታላይዝድ መደረጉ አገልግሎቶችን በሚፈለገው ልክ ተደራሽ ማድረግ እያስቻለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ዲጂታላይዝድ መደረጉ አገልግሎቶችን በሚፈለገው ልክ ተደራሽ ማድረግ እያስቻለ ነው
ባህር ዳር፤ ሰኔ 22/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የወሳኝ ኩነት ምዝገባ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲታገዝ መደረጉ አገልግሎቶችን በሚፈለገው መልኩ ተደራሽ ማድረግ እያስቻለ መሆኑ የክልሉ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አገልግሎት አስታወቀ።
የአገልግሎቱ ኃላፊ መዓዛ በዛብህ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በክልሉ የወሰኝ ኩነቶች መዝገባ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ በመደረጉ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ፍትሃዊና ተደራሽ ለማድረግ እያስቻለ ነው ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ 982 ሺህ 800 የልደት፣ የሞት፣ የጉዲፈቻ፣ የጋብቻና ፍች ኩነቶችን ለመስጠት ታቅዶ ከእቅድ በላይ 107 በመቶ ማከናወን መቻሉን ጠቅሰዋል።
የምዝገባ አገልግሎቱ ከሚሰጥባቸው ከ4 ሺህ የሚበልጡ ጣቢያዎች ውስጥ 570 የሚሆኑት በቴክኖሎጂ የተደራጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለውጤቱም ጠንካራ የቅንጅት ስራ ከመኖሩ ባለፈ በተለያዩ አማራጮች ለማህበረሰቡ የተሰጠው የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች ተጠቃሽ መሆኑን ጠቁመዋል።
የህብረተሰቡን የአገልግሎት እርካታ የማሳደግና የቴክኖሎጂ አሰራርን ተደራሽ ለማድረግና በተሻለ መልኩ ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኩነቶች ምዝገባ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲደገፍ መደረጉ የመንግስትን ወጪ ከመቀነስ ባለፈ መረጃዎችን በጥራትና በፍጥነት ተደራሽ ማድረግ ማስቻሉን ጠቅሰዋል።
በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተቀናጀ መንገድ በተሰራ ስራ ከ5 ሚሊየን በላይ ኩነቶችን መመዝገብ እንደተቻለም ኃላፊዋ አስታውቀዋል።