ቀጥታ፡

ኤንዞ ማሬስካ አዲሱ የማንችስተር ሲቲ አሰልጣኝ ሆነው በይፋ ተሾሙ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2018 (ኢዜአ):- የ46 ዓመቱ ጣልያናዊ ኤንዞ ማሬስካ በሶስት ዓመት ውል የማንችስተር ሲቲ አሰልጣኝ ሆነው ዛሬ በይፋ ተሹመዋል።

በዋንጫዎች የታጀበው የፔፕ ጋርዲዮላ የ10 ዓመታት የክለቡ ቆይታ ማብቃቱን ተከትሎ የቀድሞ ረዳቱ ማሬስካ እርሱን ለመተካት ሰፊ ግምት አግኝተው ነበር።

ማንችስተር ሲቲ ማሬስካን በሶስት ዓመት ውል መሾሙን ዛሬ ይፋ አድርጓል።

ይህም በባለፈው የውድድር ዘመን የሊግ ካፕ እና የኤፍኤ ካፕ (FA Cup) ድርብ ድል ላስመዘገበው የፕሪሚየር ሊግ ክለብ የጣሊያናዊው አሰልጣኝ ሶስተኛው የቆይታ ጊዜው ይሆናል።

ጣልያናዊው አሰልጣኝ ከሹመቱ በኋላ በሰጠው አስተያየት ማንችስተር ሲቲ በጣም ጠንቅቄ የማውቀው ክለብ ነው፤ ይህንን ቡድን የማሰልጠን ዕድል ማግኘቴ ለእኔ ድንቅ አጋጣሚ ነው ብሏል።

ማንችስተር ሲቲ በሚያስደንቅ የክለብ አመራርና አደረጃጀት ላይ የሚገኝ ቡድን ነው፤ በክለቡ ውስጥ የሚከናወኑ ማንኛቸውም እንቅስቃሴዎች አዳዲስ ፈጠራዎች የታከሉባቸው፣ የታቀዱ እና ግልጽ ዓላማን ያነገቡ ናቸው ሲል ገልጿል።

ይህ ሁኔታ ለማንኛውም አሰልጣኝ ፍጹም ስኬታማ የስራ አካባቢን ይፈጥራል፤ ስራዬን በብቃት ለመወጣት የሚያስፈልገኝን ወጥነት ይሰጠኛል ነው ያለው ማሬስካ።

ማንችስተር ሲቲ የኤንዞ ማሬስካን የአሰልጣኝነት ሹመት ለማጠናቀቅ ለቼልሲ ክለብ የ17 ሚሊዮን ፓውንድ (በግምት 22.5 ሚሊዮን ዶላር) የካሳ ክፍያ መክፈሉን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።

የተከፈለው ከፍተኛ የካሳ መጠን አሰልጣኙ ከቀድሞ ክለባቸው ቼልሲ በድንገት በመልቀቃቸው የተነሳ የተፈጠረውን የውል ውዝግብ  የቋጨ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም