የእንጦጦ-ቀበና ወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ለትውልድ የሚሻገር የልማት አሻራችን ነው - ኢዜአ አማርኛ
የእንጦጦ-ቀበና ወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ለትውልድ የሚሻገር የልማት አሻራችን ነው
አዲስ አበባ፤ሰኔ 22/2018(ኢዜአ)፦የእንጦጦ-ቀበና ወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ለትውልድ የሚሻገር የልማት አሻራችን ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
የከተማ አስተዳደሩ የእንጦጦ-ቀበና የወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ላይ ለተሳተፉ አካላት የምስጋና መርኃግብር አካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ ፤ ፕሮጀክቱ በርካታ ውጣ ውረዶችንና ፈተናዎችን አልፎ በዚህ ደረጃ በጥራትና በውበት ተጠናቆ ለምረቃ በመብቃቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
ከተማ አስተዳደሩ የጀመራቸውን ግዙፍ ሜጋ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጊዜና ጥራት የመጨረስ ትልቅ አቅም ለማሳየቱ ይህ ፕሮጀክት ማረጋገጫ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ በአይነቱ ለየት ያለ የከተማዋን የስነ-ምህዳር ሚዛን የጠበቀና ለትውልድ የሚሻገር ታላቅ ስጦታ መሆኑን በመግለጽ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን በጥንቃቄ እንዲጠብቁ አሳስበዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ሞገስ ባልቻ፤ ለብክለት ተዳርገው የነበሩትን የወንዝ ዳርቻዎች መልሶ በማልማት ወደ ሕያውና ምቹ ሁኔታ የመቀየር ሂደት ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ እንደነበር ገልጸዋል።
የእንጦጦ-ቀበና የወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ያሳየው ውጤት፣ በትክክለኛ አመራርና በትጋት ከተሠራ የማይፈታ ችግር እንደሌለ በተግባር ያረጋገጥንበት ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል የፈጠረና ለነዋሪዎች ምቹ የመዝናኛ ስፍራን ያበረከተ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በፕሮጀክቱ የተመዘገበው ስኬት የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረትና አይተኬ ሚና ውጤት መሆኑን በመግለፅ ለዚህ ውጤታማነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተሳታፊዎችና አጋር አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።