ቀጥታ፡

አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ በማድረግ ለግብርና ሥራ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ነው

ጭሮ ፤ሰኔ 22/2018(ኢዜአ)፦በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ ችግኞች የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ በማድረግ ለግብርና ሥራ ምቹ ሁኔታ እየፈጠሩ መሆኑን  የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ገለጹ።

የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐግብር በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ደረጃ በሸነን ዱጎ ወረዳ ሜይራ ሌሊሳ ቀበሌ ዛሬ ተጀምሯል።


 

በችግኝ ተከላው ላይ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ኢክራም ጠሀ እንዳሉት፤ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ እየተተከሉ ያሉ ችግኞች የተራቆቱ ተራራማ አካባቢዎች አፈር በመያዝ ምርታማ እንዲሆኑ አድርገዋል።

ኅብረተሰቡ እያገኘ ያለውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ለእንክብካቤው ተገቢውን ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራ የሀገር የወደፊት ተስፋ እንዲሁም የዛሬውና የነገው ትውልድ ጥላ በመሆኑ፣ በዚህ ረገድ በአረንጓዴ አሻራ እየተከናወነ ያለው ሥራ ይቀጥላል ነው ያሉት።

በዞኑ በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሐግብር  400 ሚሊዮን የሚጠጉ የተለያዩ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እንደሚተከሉ አስታውሰዋል።


 

በኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድ ሳኒ በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የመጪውን ትውልድ ሕይወት የተሻለ ከማድረግ አንጻር ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት ነው።

መርሃ ግብሩ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ ለእንስሳት መኖ፣ ለደን ሽፋንና ለምግብ የሚውሉ የፍራፍሬ  ችግኞች በስፋት መተከላቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም