የኢትዮጵያ እና ቻይና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እና ቻይና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ እና ቻይና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ የቻይና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ቼን ሀይን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
አምባሳደሩ በዚሁ ወቅት የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት በመጠናቀቁና ብልፅግና ፓርቲ በማሸነፉ ያስተላለፈውን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አድርሰዋል፡፡
ፓርቲው በመልዕክቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት በኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው ሰላምና መረጋጋት፣ ብሔራዊ አንድነትና ሁለንተናዊ ብልጽግና እየተረጋጋጠ እንደሚሄድ ያለውን እምነት ገልጿል፡፡
የምርጫው ውጤት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለብልፅግና ፓርቲ ያለውን ድጋፍ የሚያሳይና በቀጣይም ፓርቲው የኢትዮጵያን ሕዝቦች አስተባብሮ በመምራት ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር የማሻገር ግብን እውን እንደሚያደርግ ጠቅሷል፡፡
የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ከዚህ ቀደም የተደረሱ ስምምነቶች ተግባራዊ እንዲደረጉ መስራቱን እንደሚቀጥልና ለሁለቱ ሀገራት እድገት በየትኛውም ሁኔታ የማይናወጥ አጋርነትን እየገነባ እንደሚሄድ አረጋግጧል፡፡
አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ብልፅግና ፓርቲ በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለው የመንግስታትና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲሁም ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ጋር ያለው ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡
ሁለቱ ፓርቲዎች ሀገር በቀል በሆኑ እሳቤዎች እየተመሩ መፍትሄዎችን በማፍለቅ ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸውን ገልጸው፤ ዘርፈ ብዙ በሆኑ ጉዳዮች ተባብሮ ከመስራት ባሻገር በተለያየ መስክ እየተደረገ ላለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ያላቸውን ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አምባሳደር ቼን ሀይ በበኩላቸው በብልፅግና ፓርቲ መሪነት በመደመር እሳቤ በኢትዮጵያ እየተመዘገቡ ላሉ ድሎች ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡
በርካታ የቻይና ባለሃብቶች በተለይም በማዕድን፣ በአገልግሎት፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ በኮንስትራክሽን በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ እንደሚገኙ ነው የገለጹት፡፡
ሁለቱ ወገኖች በቀጣይ በሁሉም መስኮች የተገኙ ድሎችን ለማስቀጠልና በጋራ ለመስራት በፓርቲዎቹ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ተስማምተዋል፡፡