ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ ተኪ ምርቶችን ከማምረት ባሻገር በአካባቢ ጥበቃ ስራ ውጤታማ ተግባር አከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ ተኪ ምርቶችን ከማምረት ባሻገር በአካባቢ ጥበቃ ስራ ውጤታማ ተግባር አከናውኗል
ኮምቦልቻ፤ሰኔ 22/2018(ኢዜአ)፦የኮምቦልቻ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ተኪና ለወጪ ንግድ የሚሆኑ ምርቶችን ከማምረት ባሻገር በአካባቢ ጥበቃ ስራ ውጤታማ ተግባር ማከናወኑ ተገለጸ።
ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ በጥራት ስራ አመራር፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በስራ ላይ ጤንነትና ደህንነት ባከናወናቸው ውጤታማ ተግባራት ያገኘውን የእውቅና ሰርተፊኬት የርክክብ መድረክ ዛሬ በኮምቦልቻ ከተማ አካሄዷል።
በወቅቱም የልዩ ኢኮኖሚ ዞኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ አህመድ ሰይድ እንደገለፁት፤ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ የውጭ ምንዛሬ በማምጣት፣ ተኪ ምርት በማምረትና ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ረገድ አበረታች ውጤት አስመዝግቧል።
በተጨማሪም አሰራሩን በቴክኖሎጂ፣ በአዳዲስ እውቀትና ክህሎት የማምረት አቅም ሽግግርን ለመፍጠር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህም በጥራት ስራ አመራር፣ በአካባቢ ጥበቃ ስራ እንዲሁም በስራ ላይ ጤንነትና ደህንነት ባከናወናቸው ውጤታማ ተግባራት ከኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት የእውቅና ሰርተፊኬት ማግኘቱን ገልጸዋል።
እውቅናው ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱንና ተመራጭነቱን ከማሳደግ ባለፈ በቴክኖሎጂ የተሟላ የመሰረተ ልማት ተደራሽነት፣ በአገልግሎት ቅልጥፍና እና ጥራት የጀመረውን ስራ ዳር ለማድረስ እንደሚያስችለው አስረድተዋል።
ባለፉት 11 ወራት ብቻ 22 ሚሊዮን ብር የሚገመት ተኪ ምርት ማምረቱንም አመልክተዋል።
በተለይም የወንድ ሙሉ ሱፍ፣ ካልሲ፣ ቦርሳ፣ ክርና የተለያዩ የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶችን በማምረት የፈጠረው አቅም ለሌሎች ተሞክሮ የሚሆን ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚሻሞ ዋካሶ በበኩላቸው፣ የኮምቦልቻ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን በአመራር፣ በአካባቢ ጥበቃና ደህንነትን በማስጠበቅ ረገድ ውጤታማ ስራ ሰርቷል ብለዋል።
በዚህም የድርጅቱን መስፈርቶች አሟልቶ በመገኘቱ እውቅና መሰጠቱን ጠቁመው፣ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ የጀመራቸውን የዲጂታልና ሌሎችም ስኬታማ ተግባራት አጠናክሮ በመቀጠል ሀገርና ህዝብን ሊጠቅም እንደሚገባ አመልክተዋል።
እውቅናውም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን፣ የኢንቨስትመንት ተመራጭነቱንና የገቢ አቅሙን በማሳደግ አርዓያ ለመሆን እንደሚያስችለው አስረድተዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ፣ ውበት፣ ጽዳትና አረንጓዴ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ እጅጉ በበኩላቸው፤ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ የአካባቢን ደህንነትና ጤና በመጠበቅ ውጤታማ ተግባር አከናውኗል ብለዋል።
ይህም ምርታማነቱን በማሳደግ፣ የኢንቨስትመንት ተመራጭነቱን በማላቅና የዘርፉ ኢኮኖሚ እንዲነቃቃና ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር እንዲችል ማድረጉን ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይም የተለያዩ አመራሮችና ባለድርሻና አጋር አካላት ተገኝተዋል።