ቀጥታ፡

በዘንድሮ በጀት አመት ከ7 ሺ 7መቶ በላይ የገጠር ቤተሰቦች ከተረጂነት ወደ አምራችነት ተሸጋግረዋል

ድሬደዋ፣ ሰኔ 22/2018(ኢዜአ)፡-  በዘንድሮ በጀት አመት ከ 7 ሺህ 7 መቶ በላይ የገጠር ቤተሰቦች ከተረጂነት ወደ አምራችነት መሸጋገራቸውን  የድሬዳዋ አስተዳደር ግብርና፣ ውሃ ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ።

ተረጂነትን የሚጠየፍ አምራች ማህበረሰብ የማፍራትና በዘርፉ ለተገኙ ውጤቶች እውቅና የመስጠት ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው የተገለፀው።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ  ሚስራ አብደላ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤  ዝናብ አጠር በሆነው በድሬደዋ ገጠራማ አካባቢዎች  ማህበረሰቡ  ከጠባቂነትና ከተረጂነት ወጥቶ ምርታማ እንዲሆን በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።

ባለፉት አምስት አመታትም  በአነስተኛ መስኖ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በሰብልና በፍራፍሬ እንዲሁም በተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ የተከናወኑ ተግባራት ህብረተሰቡን ከገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ወደ አምራችነት አሸጋግሯል ብለዋል።

በተለይም የገጠሩን ክላስተር  ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የተከናወኑት ተግባራት ተረጂነት የሚጠየፍ ትውልድ በማፍራት ውጤት እንዲመዘገብበት አድርጓል ነው ያሉት።

አርብቶ አደሩ እና አርሶ አደሩ ማሕበረሰብ በተፈጥሮ ሃብቱና በተገነቡት መሰረተ ልማቶች በመታገዝ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የሚያደርገውን ጉዞ ለማሳለጥ እንዳስቻለም ነው የተናገሩት።

ለአብነትም ኡሉል ሞጆ የገጠር ቀበሌ ህብረተሰብ ሙሉ በሙሉ ከተረጂነት ወደ አምራችነት መሸጋገሩንም ነው ኃላፊዋ ያነሱት።

በዘንድሮው በጀት ዓመትም 7 ሺህ 7መቶ በላይ የገጠር ቤተሰብ ከተረጂነት ወደ አምራችነት መሸጋገራቸውን ገልጸዋል ።

በግብርና፣ በአነስተኛ የንግድ ስራዎች ሽግግር ላደረጉት አርሶ እና አርብቶ አደሮች ለስራቸው መቀላጠፍ የመነሻ ካፒታልና ሙያዊ ድጋፍ መደረጉንም አንስተዋል።

ከተረጂነት ለተሸጋገሩት የህብረተሰብ ክፍሎች በዚህ ወር መጨረሻ ዕውቅናና ሽልማት እንደሚሰጥም ነው የገለጹት።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም