የኢትዮጵያ የብዝኅ ኢኮኖሚ ዘርፍ እመርታ የዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት በማስፋት ከፍተኛ ጠቀሜታ እያስገኘ ነው - የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የብዝኅ ኢኮኖሚ ዘርፍ እመርታ የዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት በማስፋት ከፍተኛ ጠቀሜታ እያስገኘ ነው - የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ሰኔ 22/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የብዝኅ ኢኮኖሚ ዘርፍ እመርታ የዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት በማስፋት ከፍተኛ ጠቀሜታ እያስገኘ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ።
የኢትዮጵያ የብዝኅ ኢኮኖሚ ልማት አቅጣጫ በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና ዲጂታል ዘርፎች የሀገርን ዕድገት የሚያፋጥን አቅም እየፈጠሩ ይገኛል።
የብዝኅ ኢኮኖሚ የልማት አቅጣጫ እመርታዊ ውጤትም ምርታማነትን በማሻሻል፣ ንግድና ኢንቨስትመንትን በማበረታታት ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት አስቻይ ሁኔታን ፈጥሯል።
የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም በከተማና ገጠር የተፈጠረው ከፍተኛ የኢኮኖሚ መነቃቃትም በሁሉም ዘርፍ በርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚእንዲሆኑ እያደረገ ነው።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ እንዳሉት፤ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት የነበረውን ግብርና መር የኢኮኖሚ ሥርዓት ወደ ብዝኅ ዘርፍ ማሸጋገር አስችሏል።
ይህም የኢትዮጵያን የልማት አማራጮች በማስፋትና የዘርፎችን ምርታማነት በማሳደግ የኢኮኖሚ ዕድገትና ተወዳዳሪነትን የሚያሻሽል አቅም እንዲፈጠር እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በብዝኅ ኢኮኖሚ ሥርዓት ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና አይ.ሲ.ቲ. የተፈጠረው እመርታዊ ውጤትም የዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት በማስፋት ከፍተኛ ጠቀሜታ እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል።
በሌላ መልኩም ግዙፍ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች የዜችን የሥራ ዕድል በማስፋት ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ርዕይ መሰረት እየጣሉ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የከተሞች ኮሪደር፣ የቱሪዝምና የኢትዮጵያ ታምርት ሀገር አቀፍ ንቅናቄም የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማፋጠን የሚሊዮኖች ዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም የዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት በማስፋት ከኢትዮጵያ የብዝኅ ኢኮኖሚ ዘርፍ የዕድገት አማራጮች ጋር በማጣጣም በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በሚቀጥሉት ሶሰት ዓመታትም በሀገር ውስጥ 16 ሚሊየን ዜጎችን በውጭ ሀገራት ደግሞ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።