ቀጥታ፡

በዞኑ በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት አቅመ ደካማ ወገኖችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት ይከናወናሉ

ጎሮ፣ ሰኔ 22/2018(ኢዜአ)፦ በባሌ ዞን በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት አቅመ ደካማ ወገኖችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት እንደሚከናወኑ የዞኑ አስተዳደር ገለጸ። 

የዞኑ አስተዳደር የዘንድሮውን የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በአስሩ የዞኑ ወረዳዎች ዛሬ አስጀምሯል።

በዞኑ የጎሮ ከተማ የአቅመ ደካሞችን የመኖሪያ ቤት በመገንባት መርኃ ግብር ላይ በዞኑ ብልጽግና ፓርቲ የዞኑ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሴይፋዲን ሐሰን እንዳሉት፣ በባሌ ዞን ለዘንድሮው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በቂ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሥራ ተገብቷል።


 

የቤት እድሳትና ግንባታን ጨምሮ የደም ልገሳ፣ አረንጓዴ አሻራ፣ የትራፊክ አገልግሎት፣ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርትና ሌሎች ተግባራት ደግሞ ከሚከናወኑት ተግባራት ዋነኞቹ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህም ከ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚበልጡ  በጎ ፍቃደኞችን በማሳተፍ በርካታ አቅመ ደካማ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል።

በዘንድሮው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በዞኑ 14 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሚገመት አገልግሎት ለመስጠት ወደ ሥራ መገባቱንም ጠቅሰዋል፡፡

በተለይም በአገልግሎቱ የቤት ግንባታና እድሳትን ጨምሮ 2 ሺህ የሚበልጡ ቤቶችን በ60 ቀናት ለመገንባት መታቀዱን አስታውሰዋል።


 

የጎሮ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ እሸቱ ተክሌ በበኩላቸው እንዳሉት በወረዳው በየጊዜው እየተካሄደ የሚገኘው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ከማሻሻል በተጓዳኝ የህዝቡን የልማት ተሳትፎ እያጎለበተ ነው።

በዘንድሮ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በወረዳው በሚገኙ 29 ቀበሌዎች አንዳንድ የአቅመ ደካማ ቤቶች የመገንባት ሥራ ዛሬ መጀመሩንም አመልክተዋል።

የመኖሪያ ቤት ግንባታ ከተጀመረላቸው አቅመ ደካሞች መካከል አቶ አደም አሎ በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው በጎ ፍቃደኞች በአዲስ መልክ በተጀመረላቸው የመኖሪያ ቤት መደሰታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም