ጠቅላላ ምርጫው በኢትዮጵያ የሰለጠነ የዴሞክራሲ ሥርዓት ልምምድ እየጎለበተ መምጣቱን ያረጋገጠ ነው-ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላላ ምርጫው በኢትዮጵያ የሰለጠነ የዴሞክራሲ ሥርዓት ልምምድ እየጎለበተ መምጣቱን ያረጋገጠ ነው-ምሁራን
ሀዋሳ፤ ሰኔ 22/2018 (ኢዜአ)፡- በሀገሪቱ የሰለጠነ የፖለቲካ ሥርአት ከመገንባትና ዴሞክራሲን ከማጎልበት አንጻር 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የራሱን አሻራ አሳርፏል ሲሉ ምሁራን ገለጹ።
በኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት ከተካሄዱ ምርጫዎች በመራጮች ቁጥርም ሆነ በፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ እንዲሁም በቴክኖሎጂ የተደገፈ ፍትሀዊ ምርጫን በማካሄድ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተጠቃሽ ነው።
ይህም የምርጫውን ቅቡልነት በማሳደግ ለሀገረ መንግስት ግንባታና ለሰለጠነ ፖለቲካ ግንባታ ድርሻው የጎላ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገልጸዋል።
በጉዳዩ ላይ ሀሳባቸውን የሰጡ ምሁራን እንዳሉት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ የሰለጠነ የፖለቲካ ሥርአት ከመገንባት አንጻር የራሱን አሻራ ከማሳረፍ ባለፈ የዴሞክራሲ ልምምድ እየጎለበተ መምጣቱን ያረጋገጠ ነው።
በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የስነዜጋና ስነምግባር መምህር ብሩክ ደስታ እንዳሉት ምርጫ ህዝቡ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በመረጠው መንግስት ብቻ ለመመራት ያለውን ፍላጎት በግልጽ ያሳየበት ወሳኝ ሀገራዊ ሁነት ነው።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም ዜጎች ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ዕድገት የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ መሰረት መጣሉንም ጠቅሰዋል።
በምርጫው የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ስነ ምግባሩን አክብረው መንቀሳቀስና ህዝቡም በነቂስ ወጥቶ ድምጹን መስጠቱ ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ የድርሻውን ለመወጣት ያለውን ጠንካራ ፍላጎት ያሳያል ብለዋል።
እንደ መምህር ብሩክ ገለጻ የመገናኛ ብዙሀንና የሲቪክ ማህበራት በምርጫው ቅድመና ድህረ ሂደት የነበራቸው ተሳትፎ በመንግስት ጠንካራ ተቋማትን ለመገንባት የተሄደበት ርቀትን የሚያሳይ ነው።
ለዴሞክራሲ ሥርዓት መጎልበት የዴሞክራሲ ተቋማት መጠናከር ቁልፍ ድርሻ እንዳለው ገልጸው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መላውን ዜጋ ለማሳተፍ ቴክኖጂን ከመጠቀም ጀምሮ ያደረገው ዝግጅትና የመምራት አቅም የሚደነቅ ነው ብለዋል።
ህዝቡም በምርጫው በነቂስ ወጥቶ መሳተፉ ለዴሞክራሲ ሥርአት መጠናከር ካለው ፋይዳ ባለፈ በመረጠው መንግስት ብቻ እንዲተዳደርና በሀገሩም ላይ ተስፋውን እንዲያሳደግ ያደርጋል ሲሉም አክለዋል።
የምርጫው ዴሞክራሲያዊነት የመጠላለፍ ፖለቲካ እየቀረና የሀገር ፍላጎት የገባው ትውልድ እየተፈጠረ ስለመምጣቱ አመላካች ነው ያሉት ደግሞ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊና ስነሰብ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ እንዳልካቸው ጀንበሬ (ዶ/ር) ናቸው።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የህዝብ ፍላጎትና ውሳኔ የተከበረበትና የኢትዮጵያን ሰላም የማይፈልጉ የውስጥና የውጭ አካላትን ያሳፈረ መሆኑን ጠቁመዋል።
በጠቅላላ ምርጫው አሸናፊ የሆነውና በቀጣይ አዲስ መንግስት የሚመሰርተው ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ የህዝብ አደራ አለበት ያሉት መምህርና ተመራማሪው፣ በተለይ ህዝብ በተለያየ መስክ ላነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በርብርብ መስራት አለበት ብለዋል።