ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ያላቸውን ተፈላጊነትና ተወዳዳሪነት ይበልጥ ለማሳደግ ትልቅ አቅም ይፈጥራል - ኢዜአ አማርኛ
ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ያላቸውን ተፈላጊነትና ተወዳዳሪነት ይበልጥ ለማሳደግ ትልቅ አቅም ይፈጥራል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2018 (ኢዜአ):-የብሔራዊ የንግድ ጥራት መሠረተ ልማት ማጠናከሪያ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ያላቸውን ተፈላጊነትና ተወዳዳሪነት ይበልጥ ለማሳደግ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴዔታ እንዳለው መኮንን ገለጹ።
በኮሪያ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (KOICA) የሚደገፈውና የኢትዮጵያን ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ያላቸውን ተፈላጊነትና ተወዳዳሪነት ይበልጥ የሚያሳድገው "የብሔራዊ የንግድ ጥራት መሠረተ ልማት ማጠናከሪያ ፕሮጀክት" በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀምሯል።
በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ድኤታ አቶ እንዳለው መኮንን፣ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሠረት በቀለ (ዶ/ር) እና የኮይካ (KOICA) ምክትል ፕሬዚዳንት ሺን ስንግ ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ድኤታ አቶ እንዳለው መኮንን በዚሁ ወቅት፤ ፕሮጀክቱ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሚተገበር መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ የሀገሪቱን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እንዲሁም የውጭ ንግድ ተወዳዳሪነትን በከፍተኛ ደረጃ ለማጠናከር ጉልህ ሚና እንደሚኖረው አስገንዝበዋል።
ፕሮጀክቱ የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማትን አቅም በመገንባት የላብራቶሪ ምርመራና የደረጃዎች ዝግጅት ሥርዓትን ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ እንዲሆን እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
በዚህም የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች በጥራት ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ የቁጥጥርና የምርመራ አቅም ይጎለብታል ብለዋል።
አሰራሩ የአገር ውስጥ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተቀባይነት እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ፣ ደረጃቸውን ያልጠበቁና ጥራታቸውን ያልጠበቁ ምርቶች በሀገር ውስጥ እንዳይሰራጩ ለመግታት እንደሚያግዝም አመላክተዋል።
የኮሪያ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (KOICA) ምክትል ፕሬዚዳንት ሺን ስንግ በበኩላቸው፤ የተመደበው ድጋፍ በዘርፉ የተሰማሩ የጥራት መሠረተ ልማት ባለሙያዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂና አሠራር ለማሰልጠንና ብቃታቸውን ለማሳደግ የሚውል መሆኑን አረጋግጠዋል።