ኢትዮጵያን የአፍሪካና የዓለም የስፖርት ማዕከል የሚያደርጉ መሰረተ ልማቶች ግንባታ ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን የአፍሪካና የዓለም የስፖርት ማዕከል የሚያደርጉ መሰረተ ልማቶች ግንባታ ተጠናክሮ ቀጥሏል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2018 (ኢዜአ):-ኢትዮጵያን የአፍሪካና የአለም የስፖርት ማዕከል ለማድረግ የሚያስችሉ የዲፕሎማሲና የስፖርት መሰረተ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መኪዩ መሐመድ ለኢዜአ እንዳሉት ከለውጡ ወዲህ ለስፖርት ልማት ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት ዘርፈ ብዙ ለውጥ ማስመዝገብ አስችሏል።
በዓለም አቀፍ መድረኮች የኢትዮጵያን ውክልና በማሳደግ የሀገሪቱን ገጽታ ለመገንባትና የስፖርት ዲፕሎማሲን ለማጠናከር እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም 14 የሀገር አቀፍ ስፖርት ማህበራት አመራሮች በአህጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ አመራር በመሆን እያገለገሉ መሆናቸውንና ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን በዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድር መድረክ ያላቸው ተሳትፎና ውጤታማነት እያደገ መሆኑንም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ሁነቶችን እያስተናገደች መሆኗን ጠቅሰው፣ ይህም የሀገሪቱን ገፅታ ለመገንባት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።
አዲስ አበባን የአፍሪካና የዓለም ስፖርታዊ ሁነቶች ማዕከል በማድረግ ኢትዮጵያን ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለዚህም ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት መሰረተ ልማት የማስፋፊያ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አንስተው፣ አምስት ትላልቅ ስታዲየሞች የዓለም አቀፍ ስታንዳርዶችን እንዲያሟሉ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡