ሕዝቡ በምርጫው የሰጠን ድምፅ የጀመርነውን የብልፅግና ጉዞ የሚያፈጥንና የከተማዋን ዕድገት ለማስቀጠል ተጨማሪ ጉልበት የሚፈጥር ነው -ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ሕዝቡ በምርጫው የሰጠን ድምፅ የጀመርነውን የብልፅግና ጉዞ የሚያፈጥንና የከተማዋን ዕድገት ለማስቀጠል ተጨማሪ ጉልበት የሚፈጥር ነው -ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2018 (ኢዜአ):-ሕዝቡ በምርጫው የሰጠን ድምፅ የጀመርነውን የብልፅግና ጉዞ የሚያፈጥንና የከተማዋን ዕድገት ለማስቀጠል ተጨማሪ ጉልበት የሚፈጥር ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ ለከተማዋ ነዋሪዎች የምስጋና መርሐ-ግብር አካሂዷል።
በዚሁ የምስጋና መድረክ ላይ የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች ተገኝተዋል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ በመዲናዋ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እና ስኬታማ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ ነዋሪዎቹ ያሳዩት የላቀ ፅናትና ቁርጠኝነት የሚያኮራ እና የሚያስመሰግን መሆኑን ገልጸዋል።
ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ እስከ ድምጽ መስጠት ሂደት ድረስ ነዋሪዎች ያሳዩት አስደናቂ የዴሞክራሲ ተሳትፎ ታሪካዊ እንደነበርም ነው የጠቆሙት።
በምርጫው ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው ውጤት በከተማዋ የተጀመረውን የልማትና የብልፅግና ጉዞ ይበልጥ ለማስቀጠል ተጨማሪ ጉልበት እና መነቃቃት የሚሰጥ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ሌት ተቀን በታማኝነት እና በቅንነት በማገልገል፣ አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ውብና ሳቢ የማድረግ ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።