ቀጥታ፡

የሳዑዲ አረቢያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሠማራት ያላቸውን ፍላጎት ገለጹ

አዲስ አበባ፤ሰኔ 22/2018 (ኢዜአ)፦የሳዑዲ አረቢያ የተለያዩ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሠማራት ፍላጎት እንዳላቸው አስታወቁ።

በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮን መሪ አምባሳደር አወል ወግሪስ ሙሃመድ የተመራ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ልዑካን ቡድን በደማም ሁለተኛ የኢንዱስትሪ ከተማ የሚገኙትን ጆ ድሪንክስ (Jo Drinks Factory) እና ሶይል ሮስተርስ (Soil Roadsters) ፋብሪካዎችን ጎብኝቷል።

በጉብኝቱ ወቅት አምባሳደር አወል ለኩባንያዎቹ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣የኢንቨስትመንት ፖሊሲዎች እና የተቀናጁ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን (IAIPs) አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።


 

የጆ ድሪንክስ ኩባንያ ከአልኮል ነፃ የሆኑ መጠጦችን አምራች ሲሆን፣ ኩባንያው በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋዩን ለማፍሰስና ምርቶቹን ለአገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል።

ሶይል ሮስተርስ ኩባንያ ከኢትዮጵያ የጉጂ፣ ጨልጨሌ፣ ሲዳማ ቦንቤ እና ይርጋጨፌ ልዩ ቡናዎችን (Specialty Coffee) እያስመጣ የሚቆላው ፋብሪካው፤ በቀጣይ በቀጥታ ከኢትዮጵያ አምራቾችና ማህበራት ለመግዛት መወሰኑን ገልጿል።

አምባሳደር አወል ወግሪስ የሁለቱ ኩባንያዎች መሪዎች በኢትዮጵያ የቅድመ-ኢንቨስትመንት ጉብኝት እንዲያደርጉ ጋብዘዋል።

በሪያድ የሚገኘው ኤምባሲ ለጉብኝቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነ ገልጸዋል።


 

ጉብኝቱ የኢትዮጵያ እና ሳዑዲ አረቢያ ግብርና ኢንዱስትሪን ጨምሮ በንግዱ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም