ኔዘርላንድስ ከሞሮኮ ፤ ተጠባቂው የጥሎ ማለፍ ፍልሚያ - ኢዜአ አማርኛ
ኔዘርላንድስ ከሞሮኮ ፤ ተጠባቂው የጥሎ ማለፍ ፍልሚያ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ዛሬ ሶስት የ32 ኛ ዙር የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ ኔዘርላንድስ ከሞሮኮ በሞንቴሬይ ስታዲየም የሚያከናውኑት ጨዋታ የእግር ኳስ አፍቃሪያንን ትኩረት ስቧል።
ኔዘርላንድስ በምድብ ስድስት በሰባት ነጥብ መሪነት አጠናቃለች። በምድብ ሶስት የነበረችው ሞሮኮ በሰባት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች።
የሰሜን ምዕራብ አውሮፓዋ ሀገር ወደ ጥሎ ማለፍ ስትገባ የአሁኑ ለ12ኛ ጊዜ ነው።
ለሶስተኛ ጊዜ ወደ ጥሎ ማለፍ የገባችው ሞሮኮ በ22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ የደረሰች የመጀመሪያ አፍሪካዊ ሀገር በመሆን ታሪክ ሰርታለች።
ሁለቱ ሀገራት እ.አ.አ 1994 አሜሪካ ባዘጋጀችው 15ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በምድብ ምዕራፍ ተገናኝተው ኔዘርላንድስ 2 ለ 1 ማሸነፏ የሚታወስ ነው።
ሀገራቱ ከ32 ዓመታት በኋላ በዓለም መድረክ በድጋሚ ተገናኝተዋል።
ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ሞሮኮ ተገማችነቷን አስጠብቃ ለመቀጠል ጠንካራዋን ኔዘርላንድ ማሸነፍ ይኖርባታል።
በሌላኛው የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ምሽት ሁለት ሰዓት ላይ ብራዚል ከጃፓን በሂውስተን ስታዲየም ይጫወታሉ።
የአምስት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ብራዚል በምድብ ሶስት በሰባት ነጥብ መሪ ሆና በማጠናቀቅ ወደ ጥሎ ማለፉ ገብታለች።
ብራዚል በዓለም ዋንጫዋ ወደ ጥሎ ማለፍ ምዕራፍ ስትሸጋገር የአሁኑ ለ19ኛ ጊዜ ነው። በሁሉም የዓለም ዋንጫዎች የተሳተፈች ብቸኛ ሀገርም ናት።
ተጋጣሚዋ ጃፓን በምድብ ስድስት በአምስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ በዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ታሪኳ ለአምስተኛ ጊዜ ወደ ጥሎ ማለፍ መግባት ችላለች።
ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።
ከዚህ ቀደም ያደረጓቸውን ሁለት ጨዋታዎች ብራዚል በማሸነፍ የበላይነቱን ይዛለች።
ጃፓን ብራዚልን በውድድር እና በወዳጅነት ጨዋታዎች አሸንፋ አታውቅም።
ምሽት 5 ሰዓት ከ30 ጀርመን ከፓራጓይ በቦስተን ስታዲየም ይጫወታሉ።
የአራት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ጀርመን በምድብ አምስት በስድስት ነጥብ የምድቡ መሪ ሆና አጠናቃለች።
ተጋጣሚዋ ፓራጓይ በምድብ በአራት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ በምርጥ ሶስተኛነት ጥሎ ማለፉን ተቀላቅላለች።
ጀርመን ወደ ጥሎ ማለፍ ስታልፍ በዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋ ታሪክ የአሁኑ ለ14ኛ ጊዜ ነው።
ተጋጣሚዋ ፓራጓይ ወደ ጥሎ ስትገባ ለአምስተኛ ጊዜ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ጃፓን እና ኮሪያ ሪፐብሊክ እ.አ.አ በ2002 በጣምራ ባዘጋጁት 17ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በጥሎ ማለፉ ተገናኝተው ጀርመን 1 ለ 0 በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅላች። በወቅቱ እስከ መጨረሻው ተጉዛ ዋንጫውን አንስታለች።
ሁለቱ ሀገራት ከ24 ዓመታት በኋላ በድጋሚ በጥሎ ማለፍ ምዕራፍ ላይ ተገናኝተዋል።