አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ አዲስ ድንቅ ስጦታ አበርክታለች - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ አዲስ ድንቅ ስጦታ አበርክታለች - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2018 (ኢዜአ):-አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ አዲስ ድንቅ ስጦታ አበርክታለች ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የእንጦጦ-ቀበና የወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክትን በዛሬው ዕለት መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ አዲስ አበባችን የነዋሪዎቿን ጥያቄዎችና መሠረታዊ ፍላጎቶች በተጨባጭ እየመለሰች፣ ለሕዝባችን ቅድሚያ የሚሰጣቸውንና ከተማዋ የሚመጥናትን ታላላቅ የልማት ሥራዎች ሁሉ በላቀ ብቃትና ትጋት እያከናወነች ትገኛለች ብለዋል።
ዛሬ ለከተማችን አዲስ አበባ ድምቀትና ተጨማሪ ጌጥ እና የውበት ፀዳል ያላበሰውን ይህን የወንዝ ዳርቻ እና የግድብ ልማት በጠቅላይ ሚኒስትራችን ሐሳብ አመንጪነት በተሰጠን የሥራ መመሪያ መሠረት በጥራትና በፍጥነት አጠናቀን ለሕዝብ አቅርበናል ሲሉም ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ በከተማዋ ከተሰሩት ሌሎች የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶች ጋር ተዋህዶ ሲታይ በእርግጥም አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርጧ የቱሪስት መዳረሻ ብቻ ሳትሆን የውበት ማማ የሚያደርጋት ድንቅ ፕሮጀክት መሆኑን ከንቲባዋ ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ 87.6 ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን፣ 10.5 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው፤ በውስጡም እጅግ ማራኪ የሆኑ የጋራ አገልግሎት መስጫዎችንና የሕዝብ መገልገያዎችን አሟልቶ ይገኛል ብለዋል፡፡
ይህም 1 ትልቅ ግድብ፣ 16 አነስተኛ ግድቦች፣ 3 ቼክ ዳሞች፣ 1.2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ሐይኪንግ፣ እንዲሁም 20.2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የወንዝ ድጋፍ ግድግዳን (Retaining Wall) ማካተቱን አንስተዋል።
የተፈጥሮ ውበቱን ይበልጥ ለማጉላትም 3 ማራኪ ፏፏቴዎች እና 1 የውሃ ምንጭ ግንባታ የተከናወነ ሲሆን፣ የመሬት ጥበቃን ለማረጋገጥ 36,928 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው የኮንሶ ጋቢዮንና የኮንሶ እርከን ሥራዎች ተሠርተውለታል ብለዋል፡፡
ልማቱ ለተፈጥሮ በሰጠው ልዩ ትኩረት፣ 59.7 ሄክታር የሚሸፍን ውብ የአረንጓዴ ልማት ስፍራን ያበለፀገ ሲሆን፣ 50,330 የተለያየ ዝርያ ያላቸው ዛፎችም እንደተተከሉበት ገልጸዋል።
ከመሠረተ-ልማት አቅርቦት አኳያ 10.62 ኪሎ ሜትር ዘመናዊ የአስፋልት መንገድ፣ 33.2 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገዶች፣ እና 33.2 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍን ዘመናዊ የመንገድ መብራት ዝርጋታ መከናወኑን አንስተዋል።
በተጨማሪም 19.13 ኪሎ ሜትር የፍሳሽ እና የጎርፍ ማስወገጃ መስመር፣ እንዲሁም 23 ንፁህ የመጸዳጃ ቤቶች ተገንብተዋል። ጎብኚዎች ወንዙን በቀላሉና በውበት እንዲሻገሩ ለማስቻል 21 የእግረኛ ድልድዮች፣ 3 ተንጠልጣይ ድልድዮች፣ 6 የእግረኛ የብረት ድልድዮች፣ 1 ሰርኩላር ድልድይ እና 1 የኮንክሪት ድልድይ ተሠርተዋል።
ማኅበረሰቡ ዘና እንዲልና የተሟላ አገልግሎት እንዲያገኝ በማሰብም፤ 9 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ በአንድ ጊዜ 695 ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚችሉ 7 የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች (ፓርኪንጎች)፣ 4 የመሰብሰቢያ ስፍራዎች፣ 7 ፕላዛዎች እና 4 ፓቪሊዮኖች ተገንብተዋል። ለንግድና ለመዝናኛ አገልግሎት የሚውሉ 32 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ ሱቆች፣ 2 አንፊ ቲያትሮች (Amphitheaters)፣ 10 ካፌቴሪያዎች፣ 7 የልጆች መጫወቻ ስፍራዎች፣ እንዲሁም 2 አነስተኛ የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት ተካተውበታል።
ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በታለመለት የጊዜ እና የጥራት ደረጃ እንዲጠናቀቅ ሌሊት ከቀን የደከማችሁና የታተራችሁ፣ ያስተባበራችሁና የደገፋችሁ በየደረጃው የምትገኙ አመራሮች፣ እንዲሁም ለመላው የአካባቢው ማኅበረሰብ በከተማ አስተዳደሩ እና በራሴ ስም ላቅ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።