ቀጥታ፡

መንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን አካዳሚያዊ ነፃነት የሚያጎናጽፍ የራስ ገዝ አስተዳደር ሥርዓት በመዘርጋት ምቹ ዕድል ፈጥሯል 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2018 (ኢዜአ):-መንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን አካዳሚያዊ ነፃነት የሚያጎናጽፍ የራስ ገዝ አስተዳደር ሥርዓት በመዘርጋት ምቹ ዕድል መፍጠሩን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ የስራ ስምሪትና የቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  ሰብሳቢ ነገሬ ሌንጮ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።

የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስክና ደረጃዎች ያሰለጠናቸውን 2 ሺ 882 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡


 

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ የስራ ስምሪትና የቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  ሰብሳቢ ነገሬ ሌንጮ (ዶ/ር)፣ የዩንቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ተሾመ ነቃጥበብ(ዶ/ር)፣ የዩኒቨርሲቲው የሥራ አመራር ቦርድ አባላትና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ የስራ ስምሪትና የቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  ሰብሳቢ ነገሬ ሌንጮ (ዶ/ር) በሥነ-ሥርዓቱ እንደገለጹት፤ መንግስት እየሰራቸው ካሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መካከል በትምህርት ዘርፉ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል።

በዚህም መንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን አካዳሚያዊ ነፃነት የሚያጎናጽፍ የራስ ገዝ አስተዳደር ሥርዓት በመዘርጋት ምቹ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።

ምሩቃኑ በተመረቁበት የትምህርት መስክ ሀገራቸውንና ህዝባቸውን በታማኝነትና ቅንነት ማገልገል ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል።

በቀጣይም ተመራቂዎች ራሳቸውን በእውቀት በማብቃት በሀገራቸው የልማት ስራ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ  እንደሚገባም አሳስበዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ተሾመ ነቃጥበብ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የዛሬ ተመራቂዎች እዚህ መድረስ የብዙ  ድካም እና ጥረት ውጤት መሆኑን ገልፀው የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።


 

ዩኒቨርሲቲው  ስር ሰዶ የቆየውን የትምህርት ጥራት እድገት ጉድለትን ለመፍታት ሙሉ ትኩረቱ ሰጥቶ በሰራቸው ስራዎች ውጤት እያስመዘገበ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከሀገር ውስጥና ከጎረቤት ሀገራት ጭምር ተማሪዎችን በመቀበል ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት  በርካታ ምሁራንን እያፈራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዩንቨርሲቲው የፊዚክስ ትምህርት ክፍል ከፍተኛ የማዕረግ ተመራቂ ኤርሚያስ አወቀ፤  በትጋት በማጥናት ለቀጣይ ህይወቱ ስንቅ የሚሆን ከፍተኛ የትምህርት ውጤት አምጥቶ ለምርቃት መብቃቱ እንዳስደሰተው ገልጿል።


 

ሌላኛዋ ከኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል 3 ነጥብ 81 በማስመዝገብ ከፍተኛ ውጤት ምሩቅ ሰላማዊት አበራ፤ የቤተሰብ ኃላፊነትን ከትምህርት ጋር በማጣመር ከፍተኛ ውጤት አስመዝግባ በመመረቋ ኩራት እንደሚሰማት ተናግራለች። 


 

የአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል 3 ነጥብ 99 በማምጣት የማዕረግና የሜዳሊያ ተሸላሚው ሀለፎም አብርሀ በበኩሉ፤ የመምህራን እገዛና ጊዜውን በአግባቡ መጠቀሙ በከፍተኛ ውጤት ለመመረቅ መብቃቱን አንስቷል።


 

በቀጣይም በትምህርት ቆይታቸው የሸመቱትን ዕውቀትና ክህሎት ህዝባቸውንና ሀገራቸውን በታማኝነት ለማገልገል እንደሚጠቀሙበት ምሩቃኑ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም