ሸገር ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ መቆየቱን አረጋገጠ - ኢዜአ አማርኛ
ሸገር ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ መቆየቱን አረጋገጠ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ37ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ሸገር ከተማ መቻልን 2 ለ 0 አሸንፏል።
በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ፍቅሩ አለማየሁ እና ያሬድ መኮንን ግቦቹን አስቆጥረዋል።
በውድድር ዓመቱ 10ኛ ድሉን ያስመዘገበው ሸገር ከተማ በ47 ነጥብ ከነበረበት 15ኛ ደረጃ ወደ 10ኛ ከፍ ብሏል።
ዘንድሮ ከከፍተኛ ሊግ ያደገው ሸገር ከተማ በሊጉ መቆየቱን አረጋግጧል።
በሊጉ ዘጠነኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው መቻል በ56 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሃዋሳ ከተማ አንድ አቻ ተለያይተዋል።
በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ሀሰን ሁሴን በ34ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል ኢትዮ ኤሌክትሪክ መሪ ሆኗል።
ጌታነህ ከበደ በ61ኛው ደቂቃ የሃዋሳ ከተማን የአቻነት ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ51 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።
ሃዋሳ ከተማ በ50 ነጥብ ስምንት ደረጃ ላይ ይገኛል።
ዛሬ አስቀድመው በተደረጉ የ37ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሻምፒዮኑ ሲዳማ ቡና ባህር ዳር ከተማን 1 ለ 0፣ ወላይታ ድቻ አዳማ ከተማን 2 ለ 0 አሸንፈዋል።
ጨዋታዎቹን ተከትሎ 37ኛ ሳምንት ተጠናቋል።
የፕሪሚየር ሊጉ የመጨረሻ ሳምንት (38ኛ ሳምንት) መርሐ ግብር በቀጣይ ሳምንት ይካሄዳል።