ቀጥታ፡

አሰባሳቢና ገዢ ትርክት በማስረጽ ረገድ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ሚናቸውን ማጎልበት አለባቸው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2018 (ኢዜአ):- በሐረሪ ክልል አሰባሳቢና ገዢ ትርክት በማስረጽ ረገድ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ሚናቸውን ማጎልበት እንደሚገባቸው የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሔኖክ ሙሉነህ ገለፁ።

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፣ከሐረሪ ክልል ጤና ቢሮ እና ከክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር ለሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጥቷል።



የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሔኖክ ሙሉነህ፣ መልካም እሴቶች እንዲጎለብቱ እና ህዝቡ በክልሉ በሚከናወኑ ሁሉን አቀፍ ስራዎች የሚያደርገውን ተሳትፎ ማሳደግ ያስቻሉ ስራዎች  ሲከናወኑ ቆይተዋል ብለዋል።

በተለይም የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ፅንፈኛ ሀይሎች በማህበረሰቡ መካከል የሚነዙትን የጥላቻና ሀሰተኛ መረጃዎችን በመከላከል አሰባሳቢና ገዢ ትርክቶች እንዲሰርጹ በማድረግ ረገድ አበረታች  ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም አፍራሽ የሆኑ ፕሮፖጋንዳዎችን ቀድሞ በመከላከል የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅና ሕብረ ብሄራዊነት እንዲሰርፅና እንዲፀና በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ባለሙያዎች በክልሉ በሁሉም ዘርፎች ለተመዘገቡ ውጤቶች አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም አንስተዋል።

በተጨማሪም የህዝብ ሰላምና አንድነት እንዲጎለብትና የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አዎንታዊ ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ አስገንዝበዋል።




የተሰጠው የአቅም ግንባታ ስልጠናም በባለሙያዎቹ ዘንድ የሚታዩ ውስንነቶችን ለመቅረፍና ግንዛቤ ለማጎልበት ከፍተኛ እገዛ አለው ብለዋል።

ተቋሙ ለህብረተሰቡ ወቅታዊ መረጃዎችን ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ ለሚመለከታቸው አካላት መሰል ስልጠናዎች የመስጠት ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ አቶ አለምሸት ተሾመ በበኩላቸው፥ ከዩኒቨርሲቲው  የሚገኝ ዕውቀት የአካባቢውን ማህበረሰብና ተቋማት እንዲጠቅም በተለያዩ መንገዶች እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በሀረሪ ክልል ለሚገኙ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ባለሙያዎች የተሰጠው ስልጠናም የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል።




መደበኛ የሚባለው የሚዲያና የኮሙኒኬሽን ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ መረጃዎቹ ተደራሽ የሚደረግላቸው ማህበረሰቦችን ነባራዊ ሁኔት በመለየት መልዕክቶችን ማስተላለፍ እንደሚገባ አቶ አለምሸት ገልፀዋል፡፡

ይህንን ለማድረግ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች መልዕክት በመቅረፅና የማስተላለፊያ ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም ላይ ራሳቸውን ሊያበቁ ይገባል ብለዋል።

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲም የባለሙያዎቹን አቅም ለመገንባት የበኩሉን አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።

ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ስልጠና ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም