በክልሉ የፍትህ ሪፎርሙን በማሳካት አገልግሎቱን ቀልጣፋ ለማድረግ ለሰው ሀይል ልማት ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የፍትህ ሪፎርሙን በማሳካት አገልግሎቱን ቀልጣፋ ለማድረግ ለሰው ሀይል ልማት ትኩረት ተሰጥቷል
አዳማ ፤ ሰኔ 21/2018 (ኢዜአ):- በኦሮሚያ ክልል የፍትህ ሪፎርሙን በማሳካት አገልግሎቱን ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ ለሰው ሀይል ልማት ትኩረት መሰጠቱን የኦሮሚያ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ቢሮ ገለጸ ።
የኦሮሚያ ህግ ምርምርና ፍትህ ኢንስቲትዩት ለ5ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ረዳት ዳኞችና አቃቤ ህጎችን ዛሬ አስመርቋል።
የኦሮሚያ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ቢሮ ሃላፊ አቶ ጉዮ ዋሪዮ እንደገለፁት፤ ኢንስቲትዩቱ የፍትህ ሪፎርሙን ለማሳካት የሚደረገውን ጥረት በጥናትና ምርምር እንዲሁም የህግ ሙያተኞችን አቅም በማጎልበት እያገዘ ይገኛል።
በክልሉ ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በሙያና በስነ ምግባር የበቃ የሰው ሃይል ለማፍራት የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን አክለዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ አህመድ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ የክልሉን የህግ ባለሙያዎች በዕውቀትና ክህሎት በማብቃት ረገድ አበረታች ስራዎች እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በክልሉ የፍትህ ሪፎርም ለመተግበር ሙያተኞችን በማሰልጠንና በጥናትና ምርምር እየደገፈ መሆኑን ጠቁመዋል።
ቀልጣፋና ፈጣን የፍትህ አገልግሎት በመስጠት ማህበረሰቡን በታማኝነት ማገልገል ይገባል ያሉት ዳይሬክተሯ ለዚህም በስነ ምግባር የታነጸ ባለሙያ ማፍራቱን ጠቅሰዋል።
ከተመራቂዎች መካከል አቶ ጎሎልቻ ሹንዴ እንደገለፁት በቆይታቸው የህግ እውቀትን ከስነ ምግባር ጋር የሚያጣምሩበትን ዕውቀት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ ፈጣን የፍትህ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በአግባቡ እንደሚወጡ አመላክተዋል።