ቀጥታ፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካሞችን ማህበራዊ ችግሮች ለመፍታት እያገዘ ነው

ደሴ/ገንዳ ውኃ ፤ ሰኔ 21/2018 (ኢዜአ):- በደቡብ ወሎ እና በምዕራብ ጎንደር ዞኖች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካሞችን ማህበራዊ ችግሮች ለመፍታት እያገዘ መሆኑ ተገለጸ።

በዞኖቹ "በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሃሳብ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።


 

በደቡብ ወሎ ዞን በተካሄደ ንቅናቄ መድረክ ላይ የተገኙት የዞኑ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ  ቤተልሔም ብርሃኑ እንደገለጹት፣ በዞኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት አረጋግጧል።


 

ተግባሩን ለማስቀጠልም በክረምት ወራት ከ1 ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ  እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም  የአቅመ ደካሞችን ቤት የመገንባትና የመጠገን፣  ደም የማሰባሰብ  እንዲሁም የአቅመ ደካማ አርሶ አደሮችን መሬት የማልማት ሥራ ይከናወናል ብለዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአብሮነት ባህልን እያጎለበተ ነው ያሉት ደግሞ በተንታ ወረዳ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትና የወጣቶች ንቅናቄና ተሳትፎ ቡድን መሪ ወይዘሮ ባንችአለም በየነ ናቸው።


 

በተያያዘ ዜና የምዕራብ ጎንደር ዞን ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ትዕግሥት እማኘው እንደገለጹት በዞኑ በክረምቱ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ237 ሺህ በላይ ዜጎች ይሳተፋሉ።

ወጣቶች፣ ባለሃብቶች እና ህብረተሰቡን በሚያሳትፈው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር ከግማሽ ቢሊዮን ብር  በላይ የሚገመቱ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ከ280 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።


 

በአገልግሎቱም 612 መኖሪያ ቤቶችን መስራት፣ ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ የአቅመ ደካሞችን መሬት  ማልማት፣ የአረንጓዴ ልማት እንዲሁም የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግና ሌሎች በጎ ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል።  

የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እያሱ ይላቅ እንዳሉት፣ በዞኑ በበጋው ወራት የተከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች የበርካታ ወገኖችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አቃለዋል።


 

ህዝቡ በበጋ ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያከናወነውን መልካም ተግባር በክረምቱ ወቅትም በስፋት ማስቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል። 

በዞኖቹ በተከሄደ የንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ ላይ በጎ ፈቃደኞች፣ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም