የዩኒቨርሲቲው የኢንኩቤሽን ማዕከል የፈጠራና ክህሎት ውጤቶችን የምናስተዋውቅበት ምቹ ምኅዳር ፈጥሮልናል - ኢዜአ አማርኛ
የዩኒቨርሲቲው የኢንኩቤሽን ማዕከል የፈጠራና ክህሎት ውጤቶችን የምናስተዋውቅበት ምቹ ምኅዳር ፈጥሮልናል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2018 (ኢዜአ):-የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የኢንዱስትሪ ኢንኩቤሽን ማዕከል የቴክኖሎጂ ፈጠራና ክህሎት ውጤቶችን ለኢንዱስትሪዎች የሚያስተዋውቁበት ምቹ ምኅዳር እንደፈጠረላቸው የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሙያተኞች ገለጹ።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና የፈጠራ ሙያተኞችን ከኢንዱስትሪዎችና አጋሮች ጋር በቀጥታ የሚያገናኝ የፈጠራ ሥራና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ማስተዋወቂያ መድረክ ማካሄዱ ይታወቃል።
በመድረኩም በዩኒቨርሲቲው የኢንዱስትሪያል ኢንኩቤሽን ማዕከል በተማሪዎችና በተመራማሪዎች የተሰሩ የፈጠራና ክህሎት ውጤቶች ቀርበዋል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ከማል ኢብራሂም (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢንኩቤሽን ማዕከሉ ለተማሪዎችና የፈጠራ ሙያተኞች ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።
የማዕከሉ ዋና ዓላማ ተማሪዎች የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ፈጣሪና ኢንተርፕርነር የሚሆኑበትን ዓለም አቀፍ መደላድል መፍጠር መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህም የዩኒቨርሲቲው የኢንዱስትሪ ኢንኩቤሽን ማዕከል ተማሪዎችን፣ ተመራማሪዎችንና ኢንዱስትሪዎች በአንድ ቦታ የሚገናኙበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንዳስቻለ አስረድተዋል።
የስሪ ዲ ፕሪንቲንግ ዲጂታል ኮንስትራክሽን የቤት መሥሪያ ማሽን ያለሙት ዮሐንስ ረጋሳ (ዶ/ር)፤ ማዕከሉ የፈጠራ ባለቤቶችንና የኢንዱስትሪ አጋሮች በቀጥታ የሚገናኙበትን ወሳኝ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።
ለዕይታ ያቀረቡት የስሪ ዲ ዲጂታል ኮንስትራክሽን ማሽንም በኮምፒውተር የታገዘ ዲዛይንን ወደ ማሽን ቋንቋ በመቀየር በውስን የሰው ሃይል ጊዜ ቆጣቢና ጥራት ያለው ግንባታን ማከናወን እንደሚያስችል ገልጸዋል።
የሀገር ውስጥ የቴክኖሎጂ የፈጠራ አቅምን መጎልበት የአሰራር ሥርዓቶችን በራስ አቅም በማሳለጥ ዘመናዊ ተግባራትን ለማከናወን ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
ሌላኛው የፈጠራ ባለቤት ወጣት ሳሙኤል አለሙ በበኩሉ፤ በሀገር በቀል የምህንድስና ዕውቀት የለስላሳ መጠጦችን መሸጥና አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ተንቀሳቃሽ የቬንዲንግ ማሽን ማልማቱን ገልጿል።
የቬንዲንግ ማሽኑም የሁሉንም ባንኮች የክፍያ አማራጭና የደንበኞችን ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ በማንኛውም ሰዓት ያለአንዳች ኃይል መቆራረጥ ዘመናዊ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ተናግሯል።
ቬንዲንግ ማሽኑ ለትምህርትና ጤና ተቋማት ጭምር ተመራጭና ዘመናዊ አገልግሎት የሚሰጥ ነው ብሏል።
ተማሪዎችም በትምህርት ቤት ቆይታቸው የሚያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት በማጎልበት ለሚስተዋሉ የቴክኖሎጂ ክፍተቶች መፍትሔ መስጠት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝቧል።