ቀጥታ፡

ምሩቃን ሙስናን በመዋጋት ለሀገር እድገት ሊሰሩ ይገባል

ደብረ ብርሃን፤ ሰኔ 21/2018 (ኢዜአ):-ምሩቃን ሙስና እና ብልሹ አሰራርን በመዋጋት ለሀገር ዘላቂ ሰላምና የኢኮኖሚ እድገት ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው ተገለጸ።

ደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መርሀግብሮች በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 807 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።


 

በምረቃ ሥነስርአቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርና የዩኒቨርሲቲው የሥራ አመራር ቦርድ አባል መሠረት በቀለ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር፣ በምርምርና በማህብረሰብ አገልግሎት በሰራቸው ሥራዎች አበረታች ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል።

በተለይ በመማር ማስተማር ሥራው ቅድሚያ ለጥራትና ለቴክኖሎጂ ልህቀት ትኩረት በመስጠት በእውቀትና በክህሎት የዳበረ የሰው ሃይል እያፈራ መሆኑን ተናግረዋል። 

ዩኒቨርሲቲው ሀገር በኢኮኖሚና በማህበራዊ ልማት የምትፈልገውን የሰው ሃይል በብዛት፣ በአይነትና በጥራት በማቅረብ ተልዕኮውን እንዲወጣ አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል። 

የዛሬ ምሩቃንም ለሀገር  ዘላቂ ሰላም ግንባታ፣ ለኢኮኖሚ እድገትና ለብልጽግና ጉዞ ጠንክረው በመስራት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስማረ መለሰ (ዶ/ር) በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው በሀገሪቱ የኢንቨስትመንትና የኢንዱስትሪ ዘርፍ የታየውን እድገት የሚያስቀጥል የሰው ሀይል እያፈራ ነው።


 

በዛሬው እለት በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ 807 ተማሪዎችን ማስመረቁንና ከእነዚህ ውስጥ 280 የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ተመራቂዎች የህብረተሰቡን መልካም እሴትና ባህል ከማክበር ባለፈ በተሰማሩበት ቦታ ሁሉ የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል መትጋት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በተጨማሪም ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማከናወን በየዘርፉ እየተመዘገበ ያለውን እድገት ለማስቀጠል መስራት አለባችሁ ሲሉ አሳስበዋል።

በዩኒቨርሲቲው በፋርማሲ የትምህርት ክፍል 3 ነጥብ 97 ውጤት በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው ብሩክ ደግነት ፤ ሙሉ ጊዜውን ለትምህርቱ በመስጠቱ ውጤታማ ሆኖ ለሽልማት መብቃቱን ተናግሯል።


 

በማኔጅመንት የትምህርት መስክ 3 ነጥብ 9 ውጤት በማግኘት የዋንጫ ተሸላሚ የሆነችው ትርንጎ ገዛኸኝ በበኩሏ በዩኒቨርሲቲው ያገኘችውን እውቀትና ክህሎት ተጠቅማ የራሷን ሥራ ለመፍጠር ተዘጋጅቻለው ስትል ገልጻለች።


 

በምረቃ ሥነ ስርአቱ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ ተመራቂዎችና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም