ቀጥታ፡

በደቡብ ወሎ ዞን በተያዘው የመኸር እርሻ ከ224 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ይለማል

ደሴ፤ ሰኔ 21/2018 (ኢዜአ):-በደቡብ ወሎ ዞን በምግብ ራስን ለመቻልና የኢንዱስትሪ ግብአት አቅርቦትን ለማሳደግ በመኸር እርሻ ከ224 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ እንደሚለማ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ይመር ሰይድ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ዞኑ ለስንዴ ሰብል ልማት ምቹ በመሆኑ በተያዘው የመኸር እርሻ ስንዴን በስፋት ለማልማት ዝግጅት ተደርጓል።

በዚህም በክረምቱ ከ224 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ በማልማት ከ9 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል።


 

የስንዴ ልማት ምርታማነትን ለማሳደግም ከ400 ሺህ ኩንታል በላይ ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለስንዴ ልማት የተሰጠው ትኩረት አርሶ አደሩን ውጤታማ ከማድረግ ባለፈ በምግብ ራሱን ለመቻልና ለኢንዱስትሪ የሚሆን ግብአት እንዲያቀርብ ማስቻሉንም ተናግረዋል።

ስንዴን በሜካናይዜሽን፣ በኩታ ገጠም እና በአዳዲስ አሰራሮች ታግዞ ማምረት መቻሉ እየተገኘ ላለው ውጤት መሰረት መሆኑንም አመልክተዋል።

በዞኑ ጀማ ወረዳ የቀበሌ 08 ነዋሪ አርሶ አደር እንድሪስ አበበ በሰጡት አስተያየት እንዳሉት፣ ሁለት ሄክታር መሬታቸውን በስንዴ ለማልማት ማሳቸውን ደጋግመው በማረስ ለዘር ሥራ አዘጋጅተዋል።

በግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ ታግዘው በማልማትና የሰብል እንክብካቤ ሥራ በማከናወን እስከ 90 ኩንታል ምርት ለማግኘት ማቀዳቸውንም ገልጸዋል።

በዘንድሮው የመኸር ወቅት አንድ ሄክታር ተኩል ማሳቸው ላይ ስንዴ ለማልማት እንደተዘጋጁ መሆኑን የገለጹት ደግሞ  በወረኢሉ ወረዳ የቀበሌ 04 ነዋሪ አርሶ አደር አህመድ ታደሰ ናቸው። 

ቀደም ሲል ለስንዴ ልማት ብዙም ትኩረት እንደማይሰጡ አስታውሰው፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ስንዴን ማልማት ባህል በማድረጋቸው ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት በመኸር ወቅት በስንዴ ከለማው 200 ሺህ ሄክታር መሬት ከ6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም