በኦሮሚያ ክልል ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል
አዳማ ፤ ሰኔ 21/2018 (ኢዜአ):-በኦሮሚያ ክልል በበጀት ዓመቱ በተከናወኑ የልማትና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ሰፊ የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል።
በኦሮሚያ ክልል ከ3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማስመዝገብ የቻሉ 1 ሺህ 195 የሚሆኑ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ወደ ላቀ የኢንቨስትመንት ደረጃ የማሸጋገር ፕሮግራም በአዳማ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የጨፌ ኦሮሚያ የከተማ ልማት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አብዱልቃድር ሁሴን እንደገለጹት፤ ኢንተርፕራይዞቹ ከመንግሥት የተሰጣቸውን ዘርፈ-ብዙ ድጋፎችና ምቹ ፓኬጆችን በአግባቡ ወደ ተግባር በመቀየር ለዚህ ስኬትና የሽግግር ደረጃ በቅተዋል።
የክልሉ መንግሥት ድህነትን ለመቀነስ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንዲሁም የስራ አጥነት ችግርን በዘላቂነት ለመቅረፍ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ወደ ኢንቨስትመንት የተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች ባስመዘገቧቸው ስኬቶች ሳይዘናጉ፣ ይበልጥ ለላቀ ውጤት ለመብቃት በሚሰማሩበት የኢንቨስትመንት መስክ ላይ ጠንክረው መስራት እንዳለባቸውም አቶ አብዱልቃድር አስገንዝበዋል።
የኦሮሚያ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ኤባ ገርባ በበኩላቸው፤ ኢንተርፕራይዞቹ በተሰማሩባቸው የሥራ መስኮች ውጤታማ በመሆን ወደ ኢንቨስትመንት ደረጃ መሻገራቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በመጠናቀቅ ላይ ባለው የበጀት ዓመት ብቻ ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች አዲስ የሥራ ዕድል ማመቻቸት መቻሉን ኃላፊው ይፋ አድርገዋል።
ኃላፊው አክለውም፤ ወደ ሥራ ለገቡ ዜጎች ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ የብድር አቅርቦት መሰራጨቱንና ከ10 ሺህ በላይ የሊዝ ማሽነሪዎችም ለኢንተርፕራይዞቹ መሰጠታቸውን ጠቅሰዋል።
ለሥራ አጥ ዜጎች ከተፈጠሩት የሥራ ዕድሎች መካከል የጎጆ ኢንዱስትሪ፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ንግድ፣ ግብርና፣ አገልግሎት፣ ግንባታ እንዲሁም የብረታ ብረትና የእንጨት ሥራ በዋናነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በበጀት ዓመቱ ከ200 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የክልሉ ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ዕድል ማመቻቸት መቻሉን ገልጸዋል።
ወደ ሥራ ለገቡ ዜጎች የመሥሪያና መሸጫ ቦታዎች እንዲሁም ማዕከላት መተላለፋቸውን የገለጹት ኢንጂነር ኤባ፤ በዚህም ድህነትን በመቀነስ ረገድ ወሳኝ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
የአዳማ ከተማ ምክትል ከንቲባ ማቲያስ ሰቦቃ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ በከተማዋ ሥራ አጥነትን ለመቀነስና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ዘርፈ-ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በአዳማ በጎጆ ኢንዱስትሪ፣ በከተማ ግብርና በተለይም በዶሮ እርባታ፣ በወተት ላሞች ማድለብና በሰብል ልማት ዘርፎች ለሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል።