ቀጥታ፡

ህልሞቻችን እስከሚሳኩ በብርታት እንሠራለን - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2018 (ኢዜአ)፡- በሁሉም መስክ አቅደን የምንተገብራቸው ህልሞቻችን እስከሚሳኩ ድረስ በብርታት እንሠራለን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ አረንጓዴ ዐሻራ ከእሳቤ እስከ ትግበራው ኢትዮጵያ የተገለጠችበት ደማቅ ብሔራዊ ቀለም ነው ብለዋል።

በእሳቤዎች የተመሩ የታላላቅ ስልጣኔዎች እና የነጠሩ እውቀቶች ማሕደር በሆነችው ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ እሳቤ ይህ ትውልድ የአርቆ አሳቢ አባቶቹ ልጅ መሆኑን ያስመሰከረበት የጠራ ሐቅ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።




የአየር ንብረት ለውጥ በተለምዶ ከምናየው ተደጋጋሚ የኮንፈረንስ እቅድ በተሻገረ፤ አፈር ነክቶ ጭቃ ረግጦ በትጋት በመስራት የሚመጣ የትጋት ውጤት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ ከማመንጨት እስከ ትግበራ በመምራትና በመሥራት ግንባር ቀደም ሆነው አሳይተውናልም ብለዋል።

የጠራ እቅድ እና መዳረሻ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ ሀገራዊ ፕሮጀክት ከታዳጊ ህጻናት ጀምሮ የእድሜ በረከት እስከበዛላቸው አረጋውያን የተሳተፉበት ታሪካዊ የልማት ዘመቻ ሆኗል ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የኢትዮጵያ ልጆች ለዓመታት በስኬት የተገበሩት ይህ ኢኒሼቲቭ ሀገራችንን በዓለም ፊት በክብር እያስጠራ ያለ የለውጥ ምልክት እስከመሆን ደርሷል ሲሉም አስታውቀዋል።




እንደ ኮፕ 32 ያሉ ዓለም አቀፍ መድረኮችን የማስተናገድ እድሎችም በተባበረ ክንድ በተደመረ እሳቤ የመስራታችን ውጤቶች እና የብሔራዊ ዐሻራችን ሽልማቶች ናቸው ብለዋል።

በአረንጓዴ ዐሻራና በሌሎች የለውጥ ግቦቻችን የታዩ የትጋት ድል ፍሬዎች በተደመሩ ጥረቶች ኢትዮጵያ በእርግጥም እየለማች እየፈካች ትገኛለች ብለዋል።

በሁሉም መስክ አቅደን የምንተገብራቸው ህልሞቻችን እስከሚሳኩ ድረስ በብርታት እንሠራለን ሲሉም ገልጸዋል በመልዕክታቸው።

‘ተስፋን እንትከል’ ሲሉም ሕብረተሰቡ በችግኝ ተከላ በንቃት እንዲሳተፍ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም