የኢትዮጵያን ጂኦ-ስትራቴጂክ ተጠቃሚነት ለማስጠበቅ የድንበርና የኤርፖርት ደኅንነቶችን ማዘመን ወሳኝ ጉዳይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ጂኦ-ስትራቴጂክ ተጠቃሚነት ለማስጠበቅ የድንበርና የኤርፖርት ደኅንነቶችን ማዘመን ወሳኝ ጉዳይ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2018 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያን ጂኦ-ስትራቴጂክ ተጠቃሚነት ለማስጠበቅ የድንበርና የኤርፖርት ደኅንነቶችን ማዘመን ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራልና የኤርፖርትና ድንበር አስተዳደር ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።
የተቀናጀ የኤርፖርት እና የድንበር አስተዳደር ትራንፎርሜሽን ፕሮግራም ላይ ያተኮረ የምክክርና የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራልና የኤርፖርትና ድንበር አስተዳደር ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በዚሁ ወቅት፤ የትራንስፎርሜሽን ፕሮግራሙ የኢትዮጵያን የደኅንነት ስጋቶች አስቀድሞ ለመከላከል፣ የሳይበር ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና በዲጂታል ዘመን ኢትዮጵያ ያላትን ተወዳዳሪነት ለማስቀጠል ወሳኝ ነው ብለዋል።
ፕሮግራሙም ስጋቶችን በመረጃ አስደግፎ ለማወቅና ለመከላከል እንዲሁም በተቋማት መካከል የመረጃ ልውውጥን በማሳደግ ሽብርተኝነት፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች፣ የገንዘብና የመሣሪያ ዝውውርን በጋራ ለመመከት አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ፕሮግራሙ ሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎች እንዲለሙ በማድረግ የሳይበር ሉዓላዊነትን በማረጋገጥና አሰራሮች በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) እና በሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲደገፉ ግብ የጣለ መሆኑንም አስረድተዋል።
ለዚህም ስኬት የተዘጋጀው ፍኖተ-ካርታ የሚያስፈልጉትን የቴክኖሎጂ አቅም፣ የአሠራር ሥርዓቶች ስታንዳርድ፣ የሰው ሀብት፣ የመሠረተ-ልማት አቅርቦት እንዲሁም የሕግና የቁጥጥር ጉዳዮችን ለይቶ ማስቀመጡንም አብራርተዋል።
ፕሮግራሙ የሀገሪቱን የጂኦ-ስትራቴጂክ ቁመና ለማስጠበቅና የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ አንዱ ማስፈጸሚያ መሣሪያ እንደሆነ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ጂኦ-ስትራቴጂክ ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የድንበርና የኤርፖርት ደኅንነቶችን ማዘመን እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
በዚህም ሀገሪቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርግ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
ፍኖተ-ካርታው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ግቦችን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን፣ ሀገሪቱ በቀጣይ ለምታስተናግደው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ስኬት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
በመድረኩ ላይ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የጸጥታ ተቋማት መሪዎች ተገኝተዋል።