የቦንጋ ከተማን እድገትና ልማት በማፋጠን ለነዋሪቿ ምቹ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቦንጋ ከተማን እድገትና ልማት በማፋጠን ለነዋሪቿ ምቹ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ቦንጋ፤ ሰኔ 21/2018 (ኢዜአ):- የቦንጋ ከተማን ዕድገትና ልማት በማፋጠን ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የካፋ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።
የከተማ አስተዳደሩ ለቀጣይ አሥር ዓመታት ተግባራዊ የሚያደርገው የቦንጋ ከተማ ስትራክቸራል ማስተር ፕላን ላይ ያተኮረ የሕዝብ ውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
ይህ አዲስ ስትራክቸራል ፕላን የከተማዋን የመሠረተ ልማት አቅርቦት፣ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት፣ የአረንጓዴ ስፍራዎችን አጠባበቅ እና የኢንዱስትሪ ቀጠናዎችን በዘመናዊ መንገድ ለመምራት የተነደፈ መሆኑም ተገልጿል።
ዕቅዱ በቀጣይ አሥር ዓመታት ከተማዋን በፕላን በመምራት በዘፈቀደ የሚደረጉ ግንባታዎችን ለመግታትና ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ ለመዘርጋት ትልቅ መሠረት ይጥላል ተብሎም ይጠበቃል።
በመድረኩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ፤ የቦንጋ ከተማ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረች እድሜ ጠገብ ከተማ መሆኗን ተናግረዋል።
ከተማዋ ታሪኳን በሚመጥን መልኩ ሳታድግ መቆየቷን ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው፤ አሁን ላይ መንግሥት ለከተሞች ዕድገት ከሰጠው ልዩ ትኩረት በመነሳት፣ የቦንጋን ዕድገት በማፋጠን ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የከተማዋን ፕላን በአዲስ መልክ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ ከኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ጋር ውል በመግባት ሰፊ ጥናትና ምርምር ሲደረግ መቆየቱን ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።
ፕላኑ ላይ ከዚህ ቀደም የተለያዩ የውይይት መድረኮች ሲደረጉ መቆየታቸውን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፤ በዛሬው የሕዝብ መድረክ ላይ የሚሳተፉ የኅብረተሰብ ክፍሎችም አስፈላጊውን ሐሳብና አስተያየት በመስጠት ለከተማዋ ዕድገትና ልማት የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
ቦንጋ ከተማ ደረጃዋን የጠበቀችና ለነዋሪዎቿ ምቹ እንድትሆን በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተክለአብ ቡሎ(ዶ/ር) የገለጹ ሲሆን፤ አዲሱ ማስተር ፕላንም ለዚህ ስኬት ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው አስታውቀዋል።
አዲሱ ስትራክቸራል ፕላን የአካባቢውን ሥነ-ምህዳር መሠረት ያደረገ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባው፤ ከተማዋን ለልማት፣ ለመኖሪያ ቤት፣ ለንግድና ለኢንቨስትመንት ምቹ ከማድረግ ባለፈ የገቢ አቅሟን የሚያሳድግ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከዚህም ባሻገር ፕላኑ ለሕብረተሰቡን የረጅም ጊዜ የመልማት ፍላጎት ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ከንቲባው ገልጸው፤ አሁን እየተካሄደ ያለው ውይይት አስፈላጊ ግብዓቶችን በማካተት ፕላኑ በተሟላ መልኩ እንዲተገበር ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
ለሚቀጥሉት አሥር ዓመታት የሚያገለግለው ይህ አዲስ ፕላን፤ የከተማዋን ነባር 6 ሺህ 300 ሄክታር ስፋት ወደ 15 ሺህ ሄክታር በላይ ያሳደገ መሆኑ በውይይቱ ላይ ተመልክቷል።
በመድረኩ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮችና የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።