ቀጥታ፡

ለሀገራዊ ምክክሩ የተለዩ አጀንዳዎች የቆዩ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላሉ- የሀገር ሽማግሌዎች

ገንዳ ውኃ፤ ሰኔ 21/2018 (ኢዜአ):-ለሀገራዊ ምክክሩ የተለዩ አጀንዳዎች የቆዩ ችግሮችን በመፍታት ዘላቂ መፍትሄ የሚያመጡ መሆናቸውን በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውሀ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በየደረጃው ከሕዝብ ጋር ባካሄደው ተከታታይ ውይይት የቆዩ ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ዋና ዋና አጀንዳዎችን ለይቶ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡

ይህንኑ ታሪካዊ ሂደት አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የምዕራብ ጎንደር ዞን የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ለሚካሄደው ዋናው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የተመረጡት አጀንዳዎች ተገቢና ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከሀገር ሽማግሌዎቹ መካከል በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውኃ ከተማ ነዋሪ አቶ ሰጠኝ ካሴ እንደገለጹት፣ ምክክሩ ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባትና ለዘመናት ሳያግባቡ የቆዩ ችግሮችን ለመፍታት መሰረት የሚጥል ነው።

በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለጉባኤው የተለዩ አጀንዳዎች ለቆዩ አለመግባባቶች በመነጋገር ዘላቂ መፍትሄ ለማስቀመጥ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል። 

የእስካሁኑ የምክክር ሂደት አካታችና ህዝቡ በየደረጃው ተወያይቶ  ሃሳቡን በነጻነት እንዲገልጽና እንዲያንሸራሽር እድል የፈጠረ መሆኑንም የሀገር ሽማግሌው አቶ ሰጠኝ አውስተዋል።

ይህም ለግጭት መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን በሰከነ የምክክር መድረክ በመፍታት ለሀገር ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥበትን አዲስ የውይይት ባህል ለመገንባት የራሱ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል።

በሀገራዊ ምክክሩ የተለዩ አጀንዳዎች በቀጣይ የዜጎችን ሕብረ ብሔራዊ አንድነት የሚያጠናክሩ እና በጋራ ሀገር የመገንባት ሂደትን የሚያፋጥኑ ናቸው ያሉት ደግሞ በዞኑ የነጋዴ ባህር ከተማ ነዋሪና የሀገር ሽማግሌ አቶ ዳገት ከፋለ ናቸው። 

ችግሮችን በውይይት መፍታት ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለማስወገድና ፖለቲካዊ ልዩነቶች ለማጥበብ ድርሻው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

የምክክር ሂደቱ በቁርጠኝነት ከተሰራ መፍታት የማይቻል ችግር እንደማይኖር ማሳያ ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው የገንዳውኃ ከተማ ነዋሪና የሀገር ሽማግሌ ሼክ አደም ሱሌማን ናቸው።

ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሚካሄደው ዋና የምክክር ጉበኤ በኮሚሽኑ የተለዩት አጀንዳዎች የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ያገናዘቡና ለነበሩ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄን ለመስጠት ትልቅ ተስፋ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በምክክሩ አለመግባባቶችን በውይይትና በይቅርታ በመሻገር የጋራ ሀገር ለመገንባት የሚደረገው ጥረት የሁሉንም ርብርብ ስለሚጠይቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም