በጠቅላላ ምርጫው በርካታ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምክር ቤት ወንበር ማሸነፋቸው የዴሞክራሲ ምህዳሩን መስፋት ያረጋገጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጠቅላላ ምርጫው በርካታ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምክር ቤት ወንበር ማሸነፋቸው የዴሞክራሲ ምህዳሩን መስፋት ያረጋገጠ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2018 (ኢዜአ):- በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በርካታ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምክር ቤት ወንበር ማሸነፋቸው የዴሞክራሲ ምህዳሩን መስፋት ያረጋገጠ መሆኑን የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።
በክልል እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የተሻለ የሀሳብ ብዝኃነት እንዲኖርና ጠንካራ የሆኑ የመንግሥት አካላትን የመገንባት ሂደትን ለማሳካት ያስችላል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በስኬት የተካሄደውን የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።
ብልፅግና ፓርቲ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 438 መቀመጫዎችን ሲያገኝ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) 13፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ስድስት፣ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ሦስት፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ሦስት፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ ሦስት፣ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ሁለት ወንበሮችን አሸንፈዋል።
ከዚህም በተጨማሪ 10 ተፎካካሪ ፓርቲዎች እያንዳንዳቸው አንድ የምክር ቤት ወንበር አግኝተዋል።
ለክልል ምክር ቤት ደግሞ ኢዜማ 73፣ ነእፓ 35፣ ሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት 34፣ ኦብነግ 20፣ ጉህዴን 14፣ መድረክ 11፣ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት 6፣ ሕዳሴ ፓርቲ 5 እና ቤህነን 5 አግኝተዋል።
የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወይዘሮ ነቢሃ መሀመድ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በርካታ ወንበሮችን ማሸነፋቸው የፖለቲካ ምህዳሩ እየሰፋ መሆኑን ያሳያል።
በፓርላማም ሆነ በክልል የሕዝብ ምክር ቤቶች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ግብዓት የሚሆኑ ሐሳቦችን በማቅረብ ለዴሞክራሲ ሥርዓት መጠናከር የላቀ አበርክቶ እንዲኖራቸው ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
ሀገር የሚገነባው በጋራ ነው ያሉት ኃላፊዋ፤ ፓርቲዎች በርከት ባለ ቁጥር ወደ ሕዝብ ምክር ቤቶች መግባታቸው ብዝሃነት ያለው ሐሳብ እንዲስተናገድ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም አብራርተዋል።
በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መስኮች በጋራ ለመሥራት አስቻይ ሁኔታ ይፈጥራል ያሉት ወይዘሮ ነቢሃ፤ ለተቋማት ግንባታ መሳለጥ ትልቅ ምዕራፍ ከፋች ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሕዝብ ድምፅ መንግሥት ለመመስረት ብቸኛው መንገድ መሆኑን ያመላከተ መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግሥት የሚመሰረተው በኃይል ሳይሆን በሐሳብ ብቻ መሆኑን ትምህርት የሰጠ ነው ብለዋል።
ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ከምስረታው ጀምሮ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው፤ በቀጣይም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና በሀገር ሉዓላዊነት መከበር ዙሪያ መንግሥት ከሚመሰርተው ብልጽግና ፓርቲ ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራትም ውጤታማ እንዲሆኑ ፓርቲው የሚጠበቅበትን ድርሻ እንደሚወጣም አስረድተዋል።
የወሎ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ወዴፓ) ፕሬዝዳንት አቶ ነጻነት ጣሰው በበኩላቸው፤ ፓርቲዎች በሀገራዊ ጉዳይ የላቀ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የማድረግ በጎ ጅምር ሊጠናከር እንደሚገባም ጠቁመዋል።
እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ መሥራት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን መፍጠር ሀገር ለማሻገር ቁልፍ ሚና ያለው በመሆኑ፣ በዚህ ረገድ ይበልጥ ሊሰራ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።
የወሎ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ መጠናከር የበኩሉን ኃላፊነት ለመወጣት በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አመልክተዋል።
ለዚህም በተለያዩ መስኮች ለሀገር ግንባታ አበርክቶ ያላቸው የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን በጥናት ለይቶ ለማቅረብ ያልተቆጠበ ጥረት እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።
ለሀገረ መንግሥት ግንባታ መሳካት ቁልፍ መንገድ ምክክር ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ሀገራዊ ምክክሩ የታለመለትን ግብ እንዲያሳካ ፓርቲው የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።