የ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ደቡብ አፍሪካ እና ካናዳ በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ደቡብ አፍሪካ እና ካናዳ በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2018 (ኢዜአ):- የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) በዓለም ዋንጫ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ያደረገው የ32 ዙር (Round of 32) የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል።
የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብሩ ደቡብ አፍሪካ እና ካናዳ በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀመራል።
ጨዋታው ምሽት አራት ሰዓት ላይ በሎስ አንጀለስ ስታዲየም ይካሄዳል።
ደቡብ አፍሪካ በምድብ አንድ በአራት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
በተለይም በምድብ የመጨረሻ ጨዋታ ኮሪያ ሪፐብሊክን ማሸነፏ ወደ ጥሎ ማለፍ እንድትገባ አስችሏታል።
ተጋጣሚዋ ካናዳ በምድብ ሁለት በአራት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ መጨረሷ ይታወቃል።
ከዓለም ዋንጫ አስተናጋጅ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ካናዳ በምድቧ ኳታርን 6 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ያሸነፈችበት ጨዋታ በውድድሩ ታሪክ ያስመዘገበችው የመጀመሪያ ድሏ ሆኗል።
ደቡብ አፍሪካ እና ካናዳ ወደ ጥሎ ማለፍ ሲገቡ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
በዓለም ዋንጫው እርስ በእርስ ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
ከዚህ ቀደም የነበራቸው ብቸኛ ግንኙነት እ.አ.አ በ2007 በደርባን ያደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ ነው።
በወቅቱ ደቡብ አፍሪካ ቴኮ ሞዲሴ በጨዋታ እና በፍጹም ቅጣት ምት ባስቆጠራቸው ጎሎች 2 ለ 0 ማሸነፏ የሚታወስ ነው።
ሁለቱ ሀገራት ከእግር ኳስ ውጪ በዓለም መድረክ በራግቢ እና ክሪኬት ስፖርቶች ተቀናቃኝነት ያላቸው ሀገራት ናቸው።
ሀገራቱ ወደ ቀጣዩ የጥሎ ማለፍ ምዕራፍ ለመሸጋገር የሚያደርጉት ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
አሸናፊው ሀገር ወደ 16 ውስጥ መግባቱን ያረጋግጣል።
የ32 ዙር (Round of 32) የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር እስከ ሰኔ 26 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ጣምራ አዘጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ 48 ሀገራት እየተሳተፉ ይገኛል።
የተሳታፊ ሀገራት ቁጥር ወደ 48 በማደጉ ምክንያት የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) የ32 ዙር (Round of 32) የጥሎ ማለፍ ፎርማት በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ አድርጓል።
በምድብ ጨዋታዎች ወቅት 48ቱ አገራት በ12 ምድቦች (ከምድብ 1 እስከ 12) ተከፍለው ጨዋታቸውን አድርገዋል።
በ12ቱ ምድቦች አንደኛ እና ሁለተኛ የወጡ 24 ሀገራት እንዲሁም ከየምድባቸው በሶስተኛነት ካጠናቀቁት 12 ብሔራዊ ቡድኖች መካከል ስምንቱ በምርጥ ሶስተኛነት ወደ ጥሎ ማለፍ ዙሩ ገብተዋል።