ቀጥታ፡

የሊጉ ሻምፒዮን ሲዳማ ቡና ከባህር ዳር ከተማ ጋር ይጫወታል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ37ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

ባህር ዳር ከተማ ከሲዳማ ቡና በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ባህር ዳር ከተማ በ47 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል። ሻምፒዮኑ ሲዳማ ቡና በ65 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል።

ባለፉት አራት ጨዋታዎች ድል ያልቀናው ባህር ዳር ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይፋለማል።

ባህር ዳር ከተማ በሊጉ በበርካታ ጨዋታዎች (20 ጊዜ) አቻ የተለያየ ቡድን ነው።

በ36ኛ ሳምንት ከነገሌ አርሲ ጋር አንድ አቻ በመለያየት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ማንሳቱን ያረጋገጠው ሲዳማ ቡና ዓመቱን የተሻለ ነጥብ ሰብስቦ ለማጠናቀቅ የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅበታል።

በሌላኛው መርሐ ግብር ሸገር ከተማ ከመቻል ከቀኑ 10 ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ሸገር ከተማ በ44 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዟል። መቻል በ56 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።

ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ከድል የራቀው ሸገር ከተማ ካሸነፈ በሊጉ መቆየቱን ያረጋግጣል።

በ36ኛ ሳምንት ኢትዮጵያ መድንን 1 ለ 0 የረታው መቻል ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።

ከቀኑ 10 ሰዓት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከሃዋሳ ከተማ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ50 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል። ሃዋሳ ከተማ በ49 ነጥብ 19ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በ36ኛ ሳምንት ወላይታ ድቻን 2 ለ 1 በመርታት ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።

ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ሶስት ነጥብ ማግኘት ያልቻለው ሃዋሳ ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይፋለማል።

በተያያዘም ትናንት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አዳማ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በከፍተኛ ዝናብ ምክንያት ሳይካሄድ ቀርቷል።

የሊጉ አክሲዮን ማህበር ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት ጨዋታው ዛሬ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይከናወናል።

አዳማ ከተማ በ43 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዛል። ወላይታ ድቻ በ47 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በ36ኛ ሳምንት ከመቀሌ 70 እንደርታ ጋር ያለ ግብ አቻ የተለያየው አዳማ ከተማ ዛሬ ካሸነፈ በሊጉ መቆየቱን ያረጋግጣል።

በ36ኛ ሳምንት በኢትዮ ኤሌክትሪክ ሽንፈት የ2 ለ 1 ያስተናገደው ወላይታ ድቻ ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ ይጫወታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም