ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና አልጄሪያ ጥሎ ማለፉን ተቀላቀሉ - ኢዜአ አማርኛ
ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና አልጄሪያ ጥሎ ማለፉን ተቀላቀሉ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ የምድብ 10 እና 11 የመጨረሻ ጨዋታዎች ተደርገዋል።
በአትላንታ ስታዲየም በተካሄደው የምድብ 11 ጨዋታ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኡዝቤኪስታንን 3 ለ 1 አሸንፋለች።
ዮአን ዊሳ በጨዋታ እና በፍጹም ቅጣት ምት ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ፊስተን ማዬሌ ቀሪዋን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ኤልዶር ሾሙሮዶቭ የኡዝቤኪስታንን ብቸኛ ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የጨዋታ ብልጫ ነበራት።
ሁለት ግቦችን ያስቆረው ዮአን ዊሳ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጧል።
ውጤቱን ተከትሎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በአራት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቅ በምርጥ ሶስተኝነት ጥሎ ማለፏን ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀላቅላለች።
ሁሉንም የምድብ ጨዋታዎቿን የተሸነፈችው ኡዝቤኪስታን ያለ ምንም ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዛ ከውድድሩ ተሰናብታለች። ሀገሪቷ በዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ተሳትፎዋን ማድረጓ ይታወቃል።
በዚሁ ምድብ በሚያሚ ስታዲየም በተካሄደው ሌላኛው ጨዋታ ኮሎምቢያ እና ፖርቹጋል ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።
ኮሎምቢያ በሰባት ነጥብ የምድቡ መሪ ሆና ስታጠናቀቅ ፖርቹጋል በአምስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
ሁለቱ ሀገራት አስቀድመው ጥሎ ማለፍ መግባታቸው ይታወቃል።
በተያያዘም የምድብ 10 የመጨረሻ ጨዋታዎች ከእኩለ ሌሊት በኋላ ተከናውነዋል።
በካንሳስ ሲቲ በተካሄደው ጨዋታ አልጄሪያ እና ኦስትሪያ ሶስት አቻ ተለያይተዋል።
ሪያድ ማህሬዝ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ራፊክ ቤልግሃሊ ቀሪዋን ጎል ለአልጄሪያ ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ማርኮ አርናውቶቪች፣ ማርሴል ሳቢትዘር እና ሳሳ ካላድዚች የኦስትሪያን ግቦች አስቆጥረዋል።
በጨዋታው አልጄሪያ የተሻለ እንቅስቃሴ አድርጋለች
የአልጄሪያው አምበል ሪያድ ማህሬዝ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጧል።
ውጤቱን ተከትሎ አልጄሪያ በአራት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ በምርጥ ሶስተኝነት ጥሎ ማለፉን ተቀላቅላለች።
ይህንን ተከትሎም በዓለም ዋንጫ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 10 ሀገራት ያሳተፈችው አፍሪካ ከቱኒዚያ በስተቀር ዘጠኙ ሀገራት ወደ ጥሎ ማለፉ ገብተዋል።
ይህም ለአፍሪካ መልካም ስኬት የሚባል ነው።
ኦስትሪያም በተመሳሳይ አራት ነጥብ በግብ ክፍያ በልጣ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ወደ ጥሎ ማለፉ ገብታለች።
በዚሁ ምድብ ሌላኛው መርሐ ግብር አርጀንቲና ጆርዳንን 3 ለ 1 አሸንፋለች።
ሊዮኔል ሜሲ፣ ላውታሮ ማርቲኔዝ ( ፍጹም ቅጣት ምት) እና ጂኦቫኒ ሎ ሴልሶ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ሙሳ ታማሪ የጆርዳንን ብቸኛ ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
የ39 ዓመቱ ሊዮኔል ሜሲ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ወደ ስድስት በማድረስ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን አጠናክሯል።
በአጠቃላይ በዓለም ዋንጫው ከመረብ ላይ ያሳረፋቸውን ግቦች ብዛት ወደ 19 በማሳደግ የውድድሩን የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ማጠናከር ችሏል።
ለአርጀንቲናም 123ኛ ጎሉን ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ውጤቱን ተከትሎ የወቅቱ የዓለም ዋንጫ ባለቤት አርጀንቲና በዘጠኝ ነጥብ የምድቡ መሪ ሆና አጠናቃለች። ቡድኑ ቀድሞ ወደ ጥሎ ማለፍ መግባቱ ይታወቃል።
ጆርዳን ያለ ምንም ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዛ ከውድድሩ ተሰናብታለች።
ጆርዳን በዓለም ዋንጫው ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፏ ይታወቃል።
ጨዋታዎቹን ተከትሎ የምድብ መርሐ ግብር ተጠናቋል።
የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል።