ቀጥታ፡

ምሩቃን ፈጠራንና ስነ-ምግባርን በማስቀደም ለሀገር ግንባታ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል - ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 20/2018 (ኢዜአ)፦ ምሩቃን ፈጠራንና ስነ-ምግባርን በማስቀደም ለሀገር ግንባታ የበኩላቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር እና የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።

ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያስተማራቸውን 608 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።


 

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር እና የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ተመስገን ደበሎ (ዶ/ር) እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)፣ የዛሬዎቹ ተመራቂዎች ኢትዮጵያ በርካታ ችግሮችን በማለፍ አዲስ የዕድገትና የተስፋ ጎዳና በይፋ በጀመረችበት ወቅት የተመረቁ በመሆናቸው ለሀገሪቱ ተጨማሪ አቅም መሆናቸውን በአጽንኦት ገልጸዋል።

የዓለም የፖለቲካል ኢኮኖሚ በፍጥነት እየተቀያየረ ባለበት ሰዓት ወደ ሥራው ዓለም የሚቀላቀሉ ምሩቃን በመሆናቸው፤ ከዕውቀት ጋር ፈጠራን፣ ከሙያ ጋር የላቀ ሥነ-ምግባርን፣ እንዲሁም ከችሎታ ጋር ኃላፊነትን በማዋሃድ ለሀገራቸው ሁለንተናዊ ዕድገት እንዲተጉ አሳስበዋል።

በሀገሪቱ ዛሬ ላይ የሚፈለገው የተማሩ ብቻ ሳይሆኑ ተምረው የሚያሰላስሉ፣ አዳዲስ ነገሮችን የሚፈጥሩ፣ ችግርን ወደ መልካም ዕድል የሚቀይሩና በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ተገቢውን ሚና የሚጫወቱ ወጣቶችን መሆኑን ተገንዝበው የራሳቸውን ያላሰለሰ ጥረት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ተመስገን ደበሎ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ተመራቂዎቹ በተግባር ተፈትነው ለዚህ የበቁ በመሆናቸው ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለችውን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማፋጠን በቁርጠኝነትና በውጤታማነት እንዲሠሩ ጠይቀዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም ምሩቃኑ በቀሰሙት ዕውቀትና ክህሎት በመጠቀም፣ ከሙስናና ከብልሹ አሠራር በመራቅ ማህበረሰባቸውንና ሀገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት እንዲያገለግሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ዛሬ ለምረቃ ከበቁት 608 ተማሪዎች መካከል 451ዱ በመጀመሪያ ዲግሪ፣ 153ቱ በሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም አራቱ በሶስተኛ ዲግሪ (PhD) ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ መሆናቸው በምርቃቱ ወቅት ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም