የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በአቅራቢያችን መኖሩ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንድናገኝ አስችሎናል - ሸማቾች - ኢዜአ አማርኛ
የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በአቅራቢያችን መኖሩ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንድናገኝ አስችሎናል - ሸማቾች
አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 20/2018 (ኢዜአ)፦የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በአቅራቢያቸው መኖሩ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት እንዳስቻላቸው ሸማቾች ገለጹ።
መንግስት አላስፈላጊ የዋጋ ንረትን ለመከላከልና ገበያውን ለማረጋጋት የተለያዩ የግብይት አማራጮችን በመዘርጋት ሸማቾች መሰረታዊ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ የተለያዩ ተግበራት ማከናወኑ ይታወቃል።
የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ሕብረተሰቡ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ በማድረግና ገበያን በማረጋጋት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑ ይታወቃል።
ኢዜአ በተለያዩ በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች የቅዳሜና እሁድ ገበያ ስፍራዎች ላይ በመገኘት ቅኝት አድርጓል።
ሐሳባቸውን ካጋሩን አስተያየት ሰጪዎች መካከል ወይዘሮ ሰናይት ብዙአየው እንዳሉት፤ የቅዳሜና እሁድ ገበያ የተለያዩ ጥራት ያላቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያገኙበት ስፍራ ነው።
ገበያው የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም አቅም ከመፍጠር ባሻገር፣ የተለያዩ ምርቶችን በቀጥታ ማግኘት የሚያስችል በመሆኑ ተመራጭ ነው ብለዋል።
በገበያው በርካታ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረባቸው ለሕብረተሰቡ እፎይታ መስጠቱን ገልጸው ገበያው በአቅራቢያቸው መሆኑ ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል፡፡
አቶ ገዳሙ ይበልጣል እና ወይዘሮ አበበች ጎሽም በበኩላቸው፤ ገበያው ከመደበኛው ገበያ ምርቶችን ከፍተኛ ቅናሽ ያለውና የሕብረተሰቡን ገቢ ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ ለእኛ ተመራጭ ነው ብለዋል።
በአቅራቢያቸው መኖሩ የግብይት ሥርዓቱን ቀልጣፋ እና ምቹ እንዳደረገላቸው ጠቅሰው የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል።
በቅዳሜ እና እሁድ ገበያ ላይ በመሳተፍ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን የሚያቀርቡ ነጋዴዎች በበኩላቸው፤ ወደ ገበያው ለሚመጡ ሸማቾች ጥራት ያላቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ ፈቃዱ አሜጋ እና አቶ ተመቸው መቻል በሰጡት አስተያየት፤ ሸማቹ የተሻለ ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ማድረግ መቸላቻውን ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም መንግሥት የንግድ ቦታዎችን በነፃ ከማመቻቸቱ ባሻገር፣ ምርቶችን ከአቅራቢዎች በቀላሉ አግኝተው ለኅብረተሰቡ እንዲያቀርቡ ዕድል መፍጠሩንም ገልጸዋል፡፡
ይህም ምርቶችን በበቂ ሁኔታና በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ለማቅረብ ትልቅ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ በሰጡት አስተያየትም፤ መንግሰት የኑሮ ውድነትን ጫና ለመቀነስና የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡
አስተዳደሩ በከተማዋ ትላልቅ የገበያ ማዕከላትን ከመገንባት ጎን ለጎን የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን የማስፋት ስራ በመስራት በርካቶችን ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
በመካከለኛና ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ዜጎችን የኑሮ ውድነት ጫና ለማቃለል ከመደበኛው ገበያ የ20 በመቶ ቅናሽ ተደርጎ ምርቶች እየቀረቡ ሲሆን፣ ምርቶች በቀጥታ ከአምራቹ ለሸማቹ እንዲደርሱ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡