ቀጥታ፡

በወራጅ ቀጠና የሚገኘው ምድረ ገነት ሽሬ ወሳኝ ሶስት ነጥብ አገኘ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 20/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ37ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ምድረ ገነት ሽሬ ኢትዮጵያ መድንን 3 ለ 0 አሸንፏል።

ማምሻውን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አዲስ ተስፋዬ፣ ዳንኤል ዳርጌ እና አቤል ማሙሽ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ከሶስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ምድረ ገነት ሽሬ በ42 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

በሊጉ ዘጠነኛ ድሉን ያስመዘገበው ምድረ ገነት ሽሬ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት እያደረገ ባለው ትግል ወሳኝ ሶስት ነጥብ አግኝቷል።

ቡድኑ በሊጉ የመቆየት ተስፋውን ለመለምለም በመጨረሻው ሳምንት ሸገር ከተማን ማሸነፍ ይጠበቅበታል።

በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ 11ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ኢትዮጵያ መድን በ46 ነጥብ ከነበረበት 12ኛ ደረጃ ወደ 13ኛ ዝቅ ብሏል።

ዛሬ ቀን ላይ በተደረገ የ37ኛ ሳምንት ጨዋታ ሀድያ ሆሳዕና እና ድሬዳዋ ከተማ አንድ አቻ ተለያይተዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማ ከሊጉ መውረዱ ተረጋግጧል።

በተያያዘም ዛሬ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አዳማ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በከፍተኛ ዝናብ ምክንያት ሳይካሄድ የቀረ ሲሆን ጨዋታው ነገ ከረፋዱ አራት ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንደሚከናወን የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም