ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ስኬት የበኩላችንን እንወጣለን - ተመራቂ ተማሪዎች

አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 20/2018 (ኢዜአ)፦ለኢትዮጵያ የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ስኬት በተማሩበት የሙያ መስክ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በቅድመ ምረቃ፣ በድህረ ምረቃ እና በሦስተኛ ዲግሪ በመደበኛና በተከታታይ የትምህርት ፕሮግራሞች ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 246 ተማሪዎች አስመርቋል።


 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተርና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ ትዕግሥት ሀሚድ፤ ተመራቂዎች የኢትዮጵያን የዲጂታል ጉዞ ለማፋጠን ዕውቀታቸውን ወደ ፈጠራ ማሸጋገር አለባቸው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያን የዲጂታል ጉዞ ዳር ለማድረስ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ባለሙያዎችን ማፍራት ያስፈልጋል ብለዋል።


 

ሀገሪቱ አሁን ካለችበት የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ ደረጃ ከፍ እንድትል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተመራቂዎች ሚና ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ተመራቂ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀት ወደ ፈጠራና ኢንዱስትሪ ምርታማነት አቅም እንዲለውጡ በማስገንዘብ ሀገራቸውን በቅንነት እንዲያገለግሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ በበኩላቸው፤ ባለፉት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ሰፊ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።


 

ትምህርት ግቡን እንዲመታ ከተደራሽነቱ ባሻገር ጥራቱን ማረጋገጥ የግድ መሆኑን ጠቅሰው፥ መንግሥት ከቅርብ ዓመታት ውዲህ ብቁ ትውልድ ለማፍራት የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ሪፎርም አድርጎ ወደ ሥራ መግባቱን አብራርተዋል።

በዚህም ሳይንስና ቴክኖሎጂን ጨምሮ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ነው የገለጹት።

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ደረጄ እንግዳ (ዶ/ር)፤ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ሲያስመርቅ የዘንድሮው ለ12ኛ ጊዜ መሆኑን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያን የልማት ግቦች ለማሳካት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ገልጸዋል።


 

ተመራቂ ተማሪዎች በተግባር ተኮር የቴክኖሎጂ ፈጠራና በኢንዱስትሪዎች ውስጥ በሚታዩ ተጨባጭ ችግሮች ላይ ያተኮሩ ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን ማከናወናቸውን አመላክተዋል።

ዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማሳለጥ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን በእጅጉ እያሳደገ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ተመራቂ ተማሪዎች እንደ ሀገር የተጀመረው የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ግቡን እንዲመታ በተማሩበት የቴክኖሎጂ ዘርፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ተመራቂ፣ የማዕረግ ተሸላሚና የዋንጫ አሸናፊ አፎምያ ቱጋሳ፤ ለዚህ ስኬት የበቃሁት ሁሌም ለትምህርቴ ቅድሚያ ሰጥቼ መማርና ማጥናት በመቻሌ ነው ብላለች፡፡

ወደፊትም በሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ በማሽን ለርኒንግ እና በተያያዥ የቴክኖሎጂ መስኮች በመሰማራት ለሀገሯ የበኩሏን አስተዋፅኦ ለማበርከት መዘጋጀቷን ገልጻለች፡፡


 

ሌላኛዋ የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ተመራቂና የማዕረግ ተመራቂ አርሴማ ተስፋዬ በበኩሏ፣ በተማረችበት የቴክኖሎጂ ዘርፍ ሀገሯን ለማገልገል ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች፡፡

በኤሌክትሪካልና ኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ የተመረቀችው ሰሚራ አለዉ፣ ቴክኖሎጂ ለሀገር ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሳ፣ በተማረችበት የትምህርት መስክ ለሀገሯ የበኩሏን አስተዋፅኦ እንደምታበረክት ገልጻለች።


 

በአምስት ዓመት ቆይታው የህይወት ልምድና እውቀት የቀሰመ መሆኑን ጠቅሶ፤ በተማረበት ሙያ ሀገሩን ለማገልገል እንደሚሰራ የገለጸው ደግሞ የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ተመራቂ ታዴዎስ ደጀኔ ነው፡፡


 

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም