በዩኒቨርሲቲ ቆይታችን በቀሰምነው እውቀትና ክህሎት ሀገራችንን ለማገልገል ተዘጋጅተናል-ተመራቂዎች - ኢዜአ አማርኛ
በዩኒቨርሲቲ ቆይታችን በቀሰምነው እውቀትና ክህሎት ሀገራችንን ለማገልገል ተዘጋጅተናል-ተመራቂዎች
አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 20/2018 (ኢዜአ)፦በዩኒቨርሲቲ ቆይታችን በቀሰምነው እውቀትና ክህሎት ሀገራችንን ለማገልገል ተዘጋጅተናል ሲሉ የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በ2018 ዓ.ም በመደበኛ እና በተከታታይ የትምህርት መርሀ ግብሮች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና በሶስተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 817 ተማሪዎችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
ሀሳባቸውን ለኢዜአ ያጋሩ ተመራቂዎች የቀሰሙትን እውቀትና ክህሎት ለሀገር እድገትና ለህዝብ ሁለንተናዊ አገልግሎት ለማዋል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከሀገራዊ ዕድገት አንጻር የሰለጠነ የሰው ኃይል ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ፣ ለሀገር ሁለንተናዊ ብልፅግና እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
ከተመራቂዎቹ መካከል በዴቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት ቸርነት ኩሳ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ የምጣኔ ሀብት ሳይንስ ውስን የሆኑ ሀብቶችን በአግባቡ ከመምራት፣ የሕዝብን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥና ችግሮችን ከመፍታት ጋር የተያያዘ ነው።
በመሆኑም በዘርፉ በጥናትና ምርምር ላይ በማተኮር፣ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት የበኩላቸውን የጎላ አስተዋጽኦ ለማበርከት ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሌላው በአመራር ትምህርት ዘርፍ የሶስተኛ ዲግሪ ያገኙት ዮናታን አዱኛ (ዶ/ር) በትምህርት ቆይታቸው በአመራርነት ዘርፍ ሀገርን በብቃት ማገልገል የሚያስችል እውቀት፣ ክህሎትና ልምድ ማካበታቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም በሥራ ዓለም ሕዝብን በታማኝነት፣ በቅንነትና በታታሪነት ለማገልገል መነሳታቸውን ጠቁመዋል።
በሁለተኛ ዲግሪ በዴቨሎፕመንት ኮሙኒኬሽን የተመረቁት አቶ ክፍለዮሐንስ አንበርብር፤ በተለዋዋጭ ሁኔታዎች ውስጥ የሀገርን ጥቅም እና እድገት ሁልጊዜም ማስቀደም እንደሚገባ ገልጸዋል።
በተለይም የመንግሥት አገልግሎት ዘርፍ ላይ የሚሠማሩ ምሩቃን ዜጎችን በቅንነትና በአግባቡ ማገልገል እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያን ወደተሻለ የእድገት ጉዞ ለማሸጋገር መረባረብ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሰርቬይንግ ኢንጅነሪንግ ያጠናቀቁት አቶ ዘለቀ መንግስቴ በሰጡት አስተያየት፤ የተማሩትን ሙያ በየጊዜው እያሳደጉ ሕዝባቸውን በተሻለ መንገድ እንደሚያገለግሉ ገልጸዋል።
በፕሮጀክት አመራር በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቀችው ሂሩት ወልዴ፤ ሀገሯን በማገልገል የተማረችውን በተግባር ለመተርጎም መዘጋጀቷን ጠቅሳለች።