የአካል ጉዳተኞች መብትን ለማስከበርና ተጠቃሚነታቸውንም በተሻለ መልኩ ለማሳደግ በቅንጅት እየተሰራ ነው-ፌዴሬሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
የአካል ጉዳተኞች መብትን ለማስከበርና ተጠቃሚነታቸውንም በተሻለ መልኩ ለማሳደግ በቅንጅት እየተሰራ ነው-ፌዴሬሽኑ
አዳማ ፤ሰኔ 20/2018 (ኢዜአ)፡-የአካል ጉዳተኞች መብትን ለማስከበርና ተጠቃሚነታቸውንም በተሻለ መልኩ ለማሳደግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን አስታወቀ።
ፌዴሬሽኑ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮንቬንሽን አማራጭ ሪፖርት ላይ ያዘጋጀው ግብዓት ማሰባሰቢያ እና ማረጋገጫ መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ በዚህ ወቅት እንዳሉት ፤ ፌዴሬሽኑ እንደ ሀገር የአካል ጉዳተኞች መብትን ለማስከበርና አካታች በሆነ መልኩ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ በቅንጅት እየሰራ ነው።
በዚህ ረገድ መንግስት የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በአለም አቀፍ ደረጃ የወጡ ህጎች ከመቀበል አንስቶ የሀገሪቱ የህግ አካል ለማድረግ ያሳየው ቁርጠኝነት የሚያስመሰግነው መሆኑን ገልጸዋል።
ፌዴሬሽኑም ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና ድንጋጌዎች ፣ሌሎች የህግ ማዕቀፎችና መመሪያዎችንም እስከታችኛው የመንግስት መዋቅር ድረስ ተግባራዊ መሆናቸውን ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በአሁኑ ወቅትም አካል ጉዳተኞችን ማካተትና የማሳተፍ ስራ ትኩረት እንዲሰጠው ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
መንግስት በአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነት መሰረት ያከናወናቸውን ተግባራት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት ማቅረቡን ገልፀዋል።
ሪፖርቱን ተከትሎም ፌዴሬሸኑ አማራጭ ሪፖርት በመጠየቁም ጠንካራ ጎኖችን ለማበረታታት፣ የታዩ ክፍተቶች ለማሻሻልም የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱን ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።
ይህም ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች የተመቹ መሠረተ ልማቶችን ለማስፋፋትና ተደራሽ ለማድረግ፣ አካታች የሆኑ ፖሊሲዎችን ለመቅረፅ እና የተሃድሶ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለማጠናከር እንደሚረዳም ገልፀዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አህመድ ሁሴን በበኩላቸው ፌዴሬሽኑ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ምክር ቤቱ ጠንካራ አጋር መሆኑን ተናግረዋል።
በሀገሪቱ አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚወጡ አዋጆች እና ሕጎችን መሰረት አድርጎ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በፖለቲካ ጉዳዮች መብቶቻቸው ለማስጠበቅ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
መንግስትም ለዘላቂ የልማት ግቦች ስኬታማነት አካል ጉዳተኞችን ትርጉም ባለው መንገድ ተጠቃሚ ለማድረግ አበክሮ እየሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
በመድረኩ ላይ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ አካል ጉዳተኞች ማህበራትና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።