ቀጥታ፡

ድሬዳዋ ከተማ ከሊጉ የወረደ ሶስተኛ ቡድን ሆኗል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 20/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ37ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ሀዲያ ሆሳዕና እና ድሬዳዋ ከተማ አንድ አቻ ተለያይተዋል።

በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ብሩክ በየነ በ44ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል ሀዲያ ሆሳዕና መሪ ሆኗል።

አቤል ነጋሽ በ56ኛው ደቂቃ ከመረብ ላይ ያሳረፈው ግብ ድሬዳዋ ከተማን አቻ አድርጓል።

ውጤቱን ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማ አንድ ጨዋታ እየቀረው በ39 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ወርዷል።

ድሬዳዋ ከተማ ከሊጉ የወረደው ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ነው።

አርባምንጭ ከተማ እና መቀሌ 70 እንደርታን ተከትሎ ከሊጉ የወረደ ሶስተኛ ቡድን ሆኗል።

ቀሪ የሚወርደው አንድ ክለብ በቀሪ ጨዋታዎች የሚለይ ይሆናል።

ነጥብ የተጋራው ሀዲያ ሆሳዕና በ47 ነጥብ ደረጃውን ከ13ኛ ወደ 11ኛ ከፍ አድርጓል።

በተያያዘም ዛሬ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አዳማ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በከፍተኛ ዝናብ ምክንያት ሳይካሄድ ቀርቷል።

ጨዋታው ነገ ከረፋዱ አራት ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንዲደረግ መወሰኑን የሊጉ የውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም