ቀጥታ፡

የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ማህበረሰቡ የሚቀላቀሉ የቀድሞ ታጣቂዎች የሰላም አምባሳደር መሆን አለባቸው -የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን

ቢሻን ጉራቻ፤ ሰኔ 20/2018 (ኢዜአ):- የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ማህበረሰቡ የሚቀላቀሉ የቀድሞ ታጣቂዎች በማህበረሰቡ ውስጥ የለውጥ ፋና ወጊ እና የሰላም አምባሳደር መሆን እንዳለባቸው የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አስገነዘበ።

በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩና የመንግስትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ በማቋቋም ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉም ተገልጿል።


 

ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎች በቢሻን ጉራቻ ማዕከል የወሰዱትን የተሃድሶ ስልጠና አጠናቀው ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል መርሃ ግብር አካሂዷል።

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን በመርሃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት፤ የሰላም ጥሪ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ መደበኛ ህይወት እየተመለሱ ነው።

ከህዳር 2016 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ባለው ጊዜ ውስጥ በተለያዩ ክልሎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩና የሰላም አማራጭን የተቀበሉ በርካታ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ሰላማዊ ህይወት መመለሳቸውን ገልጸዋል።

የዛሬዎቹን ጨምሮ በኦሮሚያ ክልልም የሰላም ጥሪ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀላቸውን ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።

የክልሉ መንግስት የቀድሞ ታጣቂዎች በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ተሰማርተው ውጤታማ እንዲሆኑ የወሰደውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።

በዛሬው ዕለት ስልጠናውን አጠናቀው ወደ ማህበረሰቡ የሚቀላቀሉ የቀድሞ ታጣቂዎች በማህበረሰቡ ውስጥ የለውጥ ፋና ወጊ እና የሰላም አምባሳደር መሆን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል የሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ኤባ ገርባ በበኩላቸው፤ የሰላም አማራጭ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች በዘላቂነት ህይወታቸውን እንዲመሩ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የሰላም አማራጭ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም በ265 ኢንተርፕራይዞች በማደራጀት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

በዛሬው ዕለት የተሃድሶ ስልጠና ያጠናቀቁትንም በቀጣይ ህይወታቸውን በዘላቂነት የሚመሩበትን ሂደት የማመቻቸት ስራ መሰራቱንና የሚደረገው ክትትልና ድጋፍ እንደሚጠናከር አስረድተዋል።

ከባሌ አካባቢ የመጣውና በተሃድሶ ስልጠና ውስጥ ያለፈው አብድራዛቅ ነገዎ፤ በተሳሳተ መረጃ በጫካ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ተናግሯል።

"ለኦሮሞ እንታገላለን ብለን ህዝቡን ለከፋ አደጋ ነው የዳረግነው" ያለው የቀድሞው ታጣቂ ፤ የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል የበደለውን ህዝብ ለመካስ መዘጋጀቱን ገልጿል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አመራሮች እና ሰራተኞች እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ አባገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም