መንግስት የትምህርት ዘርፉን ጥራትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ በሰጠው ትኩረት የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የትምህርት ዘርፉን ጥራትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ በሰጠው ትኩረት የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ ነው
ጅግጅጋ፤ ሰኔ 20/2018 (ኢዜአ)፦ መንግሥት የትምህርት ዘርፉን ጥራትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ በሰጠው ትኩረት የተሻለ ውጤት መመዝገቡን የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 672 ተማሪዎች በዛሬው እለት አስመረቋል።
በወቅቱም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ትምህርት የእድገት ሁሉ መሠረት፣ ማህበረሰብን የሚገነባና የአስተሳሰብ ለውጥን በማምጣትም ረገድ የማይተካ ሚና አለው።
ለዚህም መንግሥት የትምህርት ዘርፉን ጥራትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ በሰጠው ልዩ ትኩረት የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ መምጣቱን ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት ከተከናወኑ ቁልፍ ተግባራት መካከል ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ ብቃት ያላቸው ዜጎችን ለማፍራት የተሰራው ስራ በአዎንታ የሚታይ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ አበረታች ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አካዳሚያዊ ነፃነታቸውንና ራሳቸውን በራስ የማስተዳደር መብታቸውን በማረጋገጥ፣ ውጤትን ማዕከል ያደረገ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ሥርዓት እየተገነባ መሆኑን ገልጸዋል።
ተመራቂዎች በሚሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ውጤታማ በመሆን የሀገራቸውን ዕድገትና ልማት የማስቀጠል ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል።
የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ኡስማን በበኩላቸው ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የቀሰሙትን እውቀትና ክህሎት ወደ ተግባር በመቀየር ለሀገር ልማትና ብልጽግና ሊያውሉ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ትምህርት የእድገት መሠረት በመሆኑ ልዩ ትኩረት በመስጠት ሲተገበር መቆየቱን ገልጸው፤ በሁሉም መስክ የተማረ የሰው ኃይልን ለማፍራት እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል።
የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሰኢድ መሀመድ (ዶ/ር)፤ ዩኒቨርሲቲው በሰው ኃይል ልማት ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም በያዝነው የትምህርት ዘመን ዩኒቨርሲቲው በሁሉም መርሃ ግብሮች በአጠቃላይ ከ16 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዩኒቨርሲቲው የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩን ችግር የሚፈቱ በፍላጐት ላይ የተመሠረቱ የጥናትና ምርምር እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎችን በትኩረት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይም የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የተመራቂ ተማሪዎች ቤተሰቦች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።