ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ ለውይይት ያቀረባቸው አጀንዳዎች ሰላምና አብሮነትን የሚያጠናክሩ ናቸው- ምሁራን

ሚዛን አማን፣ ሰኔ 20/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለውይይት ያቀረባቸው አጀንዳዎች መሠረታዊ ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ሰላምና አብሮነትን የሚያጠናክሩ መሆናቸውን ምሁራን ተናገሩ፡፡

ኮሚሽኑ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ/ም ጀምሮ ለሚካሄደው ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ የሚቀርቡ 8 አጀንዳዎችን ለይቶ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ይህንን በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ምሁራን እንደገለፁት፤ ኮሚሽኑ ይፋ ያደረጋቸው ዋና ዋና አጀንዳዎች ከዚህ ቀደም የነበሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያስችሉ ሐሳቦችን የያዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዚሀም በኮሚሽኑ ለውይይት የቀረቡ አጀንዳዎች የኢትዮጵያን መሠረታዊ ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ሰላምና አብሮነትን የሚያጠናክሩ ናቸው ሲሉም አክለዋል።

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ አማረ ፈንታው (ዶ/ር) እንዳሉት የፖለቲካ ሥርዓቱን ከኃይል እሳቤ ለምክክር ወደ መድረክ ማምጣት መቻል ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት ነው።

ኮሚሽኑ ለይቶ ያቀረባቸው አጀንዳዎች የኢትዮጵያን መሠረታዊ ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ሰላምና አብሮነትን የሚያጎለብቱ መፍትሔዎችን የሚያመጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

''ለራሳችን ችግሮች በራሳችን መፍትሔ ለማምጣት በጠረጴዛ ዙሪያ የመቀመጥ ዕድል መፈጠሩ ለኢትዮጵያ ወሳኝ የታሪክ በርን የሚከፍትና ወደፊትም በትውልድ የሚወሳ የታሪክ አካል ይሆናል'' ብለዋል።

ለውይይት የቀረቡት ስምንቱ ዋና ዋና አጀንዳዎች በንዑስ አጀንዳነት በርካታ ዝርዝር ጉዳዮችን እንደሚያነሱ ገልጸው ኮሚሽኑ የአካታችነትን መርህ ተግባራዊ በማድረግ ምክክሩን ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ማድረሱ ትልቅ ተቋማዊ ስኬት እንደሆነም አክለዋል።

ከዚህ ቀደም ይህ ሥርዓት ባለመሞከሩ ብዙ ስብራቶች ገጥመውናል ያሉት ተመራማሪው በብዙ ድካምና ትዕግስት  የተፈጠረው የምክክር መድረክ "የሥነ ልቦናና የሞራል ከፍታችን ማረጋገጫ ነው" ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ቢመርቅ በርሁን በሀገራችን በፖለቲካ እና ሌሎች ምክንያቶች የተፈጠሩ መሠረታዊ ችግሮችን ለመፍታት የተለዩ አጀንዳዎችን በአግባቡ ወደ ውጤት መቀየር ከሁሉም ዜጋ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።

ወደ ምክክር መድረክ የመጡትን የተቋም ግንባታ፣ የሕግ የበላይነት እና ሌሎች ጉዳዮች በውይይት ቋሚ መሠረት ማስያዝ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደትን በተጠናከረ ሁኔታ ለማስኬድ ያስችላል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም