በክልሉ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተከናወኑ ተግባራት ምርታማነት እንዲጨምር አስችለዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተከናወኑ ተግባራት ምርታማነት እንዲጨምር አስችለዋል
ጎጀብ፤ ሰኔ 20 /2018 (ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተከናወኑ ተግባራት ምርታማነት እንዲጨምር ማስቻላቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ክልላዊ የ2018 ዓ.ም የክረምት ወራት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ተከላን ''ተስፋን እንትከል'' በሚል መሪ ሐሳብ በካፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ ጎጀብ ቀበሌ በመገኘት በይፋ አስጀምረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት፤ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የተተከሉ ችግኞች የአፈር መሸርሸርን በመከላከል፣ እርጥበታማ የአየር ሁኔታ እንዲጨምር አድርገዋል።
እንዲሁም የከርሰ ምድርና ገፀ ምድር የውሃ ሀብት ክምችት በመጨመሩ ምርታማነት እንዲያድግ አስችለዋል ብለዋል።
በዘንድሮው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከበፊቱ በተለየ መልኩ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሻይ ቅጠል ችግኞች የሚተከሉ መሆኑን ጠቁመው ይህም ለክልሉ ተደማሪ አቅምን እንደሚፈጥር አመልክተዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ኢያሱ ኤልያስ በበኩላቸው በቀደሙት ጊዜያት በነበረዉ የተዛባ እይታ የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን በተገቢና በዘላቂነት መጠቀም አልቻልንም ብለዋል።
በዚህም ሳቢያ ሀገራችን በምግብ ራሷን መቻል አቅቷት ተመፅዋች ሆና መቆየቷን ገልጸው ይህን ታሪክ በመቀየር ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ፣ የመሬትና ሌሎች ሀብቶቿን በዘላቂነት ለመጠቀም ባለመ በተቀረፀው የአረንጓዴ አሻራ ኢንሼቲቭ ዘርፈ ብዙ ውጤቶች ተመዝግበዋል ነው ያሉት፡፡
በዚህም ምርታማነት ጨምሯል፤ የአፈር ለምነት አድጓል፤ የቡናና የፍራፍሬ ልማት አድጓል፤ በቤተሰብ ደረጃ የተመጣጠነ ምግብ የማግኘት ሁኔታም እያደገ መምጣቱን ነው የጠቀሱት፡፡
በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ ኢንሼቲቭ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን የገለፁት ደግሞ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ናቸው፡፡
ኢንሼቲቩ የክልሉን ስነ-ምህዳር በከፍተኛ ሁኔታ መቀየሩን ጠቁመው ጠፍተው የቆዩ አዕዋፋትና የዱር እንስሳት እንዲመለሱና የደረቁ ምንጮች እንዲጎለብቱ ማስቻሉን ገልፀው የክልሉን የደን ሽፋን ከ41 ወደ 43 በመቶ ማሳደግ ችሏል ብለዋል።
የ2018 ዓ.ም በክልሉ በአጠቃላይ 460 ሚሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉ ጠቅሰው ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ እንደሚተከሉም ተናግረዋል።
የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንደሻው ከበደ በበኩላቸው የአየር ንብረት ለውጥ የዜጎችን ህይወት እየፈተነ ባለበት ወቅት የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ሁነኛ መፍትሔ ተደርጎ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የዞኑ ማህበረሰብ ደንን ጠብቆ የማቆየት ልምዱን ከአረንጓዴ አሻራ ዕሳቤ ጋር በማጣመር የደን ሽፋኑ ላይ ከፍተኛ እመርታ እየፈጠረ እንደሚገኝ ጠቁመው በዞኑ በያዝነው ክረምት ወራት የተለያዩ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ይተከላሉ ብለዋል።