በከተማና መሠረተ ልማት ዘርፍ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተግባራት ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በከተማና መሠረተ ልማት ዘርፍ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተግባራት ተከናውነዋል
አርባ ምንጭ፤ ሰኔ 20/2018 (ኢዜአ)፦ በበጀት ዓመቱ በከተማና መሠረተ ልማት ዘርፍ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ አበይት ተግባራት መከናወናቸውን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ አስታወቁ።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማን በአርባ ምንጭ ከተማ ማካሄድ ጀምሯል።
ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ፤ መንግሥት ለከተሞች ዕድገትና መስፋፋት እንዲሁም ለዜጎች ሕይወት መቃናት በልዩ ትኩረት እየሠራ በመሆኑ፣ ዘመኑ የከተሞች የትንሣኤ ዘመን ነው ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ በተቋማዊ የማስፈጸም አቅም፣ በሀብት አጠቃቀም እና በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ሰፊ ማሻሻያዎች መደረጋቸውንም ገልጸዋል።
ከተሞችን የብልጽግና ተምሳሌት ማድረግ የተቻለ ሲሆን፣ የሥራ ባሕላችንን በመቀየር ተወዳዳሪነትን ማሳደግ ተችሏልም ነው ያሉት።
ከዚህም ባለፈ በከተሞች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸው፤ በቤቶች ልማት ዘርፍም ሰፊ ለውጥ እየተመዘገበ ይገኛል ብለዋል።
በቀጣይም ከተሞች ከድህነት፣ ከጉስቁልና፣ ከሥራ አጥነት እና ከመልካም አስተዳደር ችግሮች ወጥተው፣ የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ እንዲፋጠን በትኩረት እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ መስፍን መንዛ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ከተማዋ ባላት የተፈጥሮ ጸጋ ልክ ለማደግ ሩቅ አልማ እየተጋች መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ቱሪዝምን የልሕቀት ማዕከል ባደረገ መልኩ መጠነ ሰፊ ልማቶች እየተከናወኑ ሲሆን፣ የኮሪደር ልማቱም የከተማዋን ተወዳዳሪነትና ውበት ይበልጥ ገልጦ እያሳየ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚሁ የአፈጻጸም ግምገማ መድረክ ላይ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ የፌዴራልና የክልል እንዲሁም የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።